Fana: At a Speed of Life!

ከ355 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን ከ355 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ 254 ሚሊየን የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና 101 ነጥብ 8 ብር የወጭ፤ በድምሩ 355 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዙን ገልጿል፡፡

ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር የላቀ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

በዚህም ÷ ድሬድዋ፣ ሐዋሳ እና አዋሽ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በቅደም ተከተላቸው 92 ሚሊዮን፣ 48 ሚሊዮን እና 33 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን በመያዝ ከፍተኛውን ድርሻ ወስደዋል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ መያዛቸውም ነው የተገለጸው፡፡

የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋዉሩ የተገኙ ሶስት ግለሰቦች እና አራት ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.