Fana: At a Speed of Life!

ለኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል በኦማን ለመፍጠር የሚያስችል ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ውይይት ከኦማን የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ኃላፊዎች ጋር ተካሄደ፡፡

የሥራና ክኅሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ÷ የውይይቱ ዓላማ አዲስ ስምምነት በመፈፀም ለኦማን የሰለጠነና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል ማቅረብ መሆኑን ተናግረዋል።

በኦማን የሠራተኞች ጉዳይ ኃላፊዎች በበኩላቸው ÷ ኦማን መብታቸውን አስጠብቃ የምታሠራቸው ሠራተኞች ከኢትዮጵያ እንደምትፈልግ አስረድተዋል፡፡

ለተፈጻሚነቱም የቀድሞውን ሥምምነት ማደስ አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ የሥምምነት ሠነድ ማዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።

አቶ ንጉሡ ወደ ኦማን ለሥራ የሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ዜጎች መብት እንዲጠበቅ ያዘጋጁት ረቂቅ ሠነድ በኅግ ባለሙያዎች በጥልቀት ታይቶ ሐሳብ ተሠጥቶበት በኤምባሲዎች በኩል የሚፈፀም ይሆናል ብለዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ÷ ወደተለያዩ ሀገራት የሠለጠነና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል በመላክ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሠራ እንደሚገኝ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ሚኒስቴሩ ከኦማን በተጨማሪ ከሌሎች የተለያዩ ሀገራት ጋርም ስምምነቶች እየፈፀመ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

77 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አረብኛ ቋንቋን ጨምሮ ሊሠሩ በሚችሉበት ሙያ ለማሰልጠን ዝግጁ መሆናቸውን አቶ ንጉሡ ጥላሁን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ የቤት ውስጥ ሠራተኛ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ሙያዎች የተመረቁ ባለሙያዎችን ለዓለም አቀፉ የሥራ ገበያ ለማቅረብ እየሠራች መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ከኦማን የመጡት የሥራ ኃላፊዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ያበለፀገውን የመረጃ ሥርዓት ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው ቢሮ ተገኝተው ጎብኝተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.