Fana: At a Speed of Life!

በካራማራ ታንክ ማራኪው ጀግና ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የካራማራው ጀግና አሊ በርኬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡

ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በ72 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ጀግናው አሊ በርኬ የቀድሞው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል የነበሩ ሲሆን ፥ እናት ሀገር ተወራለች ዝመት በተባሉበት የልጅነት ዕድሜያቸው የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር እና ወራሪውን የዚያድባሬን ጦር ለመመከት ከእኩዮቻቸው ጋር ዘምተዋል።

የሶማሊያው ዚያድባሬ ጦር እስከ አፍንጫው ታጥቆ የመስፋፋት ህልሙን ለማሳካት ኢትዮጵያን ሲወር፥ አሊ በርኬ እና ጓደኞቻቸው ግንባር በመዝመት ምንጊዜም የሚታወሰውን የካራማራ ጦርነት በድል ተወጥተዋል።

በወቅቱ የዚያድባሬን ወረራ ለመመከት የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም፥ ሚያዚያ 4 ቀን 1969 ዓ.ም የእናት ሀገር አድን ጥሪን አውጀው ነበር።

ጀግናው ሻለቃ አሊ በርኬም ጥሪውን በመቀበል ከቀድሞው ወለጋ ክፍለ ሀገር አሶሳ አውራጃ ቤጊ ወረዳ  ወደ ኦጋዴን ዘምተዋል።

በዚህም በኦጋዴን አቡሸሪፍ ግንባር በተደረገ ከባድ ውጊያ የወራሪውን የሶማሊያ ሀይል ቲ-55 ታንኮች በእጅ ቦምብ ደጋግመው በማጋየት ማርከው ትልቅ ጀብድ ሰርተዋል።

በዚህ ጦርነት ኢትዮጵያ በእነ አሊ በርኬና ሌሎች ጀግና ኢትዮጵያውያን ታላቅ ተጋድሎ በታላቁ የካራማራ ድል ሉዓላዊነቷን አስከብራ ቆይታለች፡፡

በጦር ሜዳ ግብራቸውም ጀግና ተብለው የኒሻን ሽልማት ተበረከተላቸው፡፡

ሆኖም ይህ ሽልማትና ክብር ብዙ አልቆየም ፤ ኢትዮጵያን ከወራሪ ሀይል ለመታደግ የተጋደሉት ሰው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከዘጠኝ ዓመታት በላይ ታስረው ቤተሰባቸውም ተበተነ፡፡

የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ አሊ በርኬ እስር ቤት ከዘጠኝ ዓመት በላይ በእስር መቆየታቸውም ግድ ሆነ፡፡

ከእስር ሲወጡም የሚገባቸውን ክብር ሳያገኙ መቆየታቸውና የሰሩትን ያክል ሳይሆን ተቃራኒ ህይወት ማሳለፋቸው ይነገራል፡፡

በቦምብ ታንክ ማራኪው የካራማራው ጀግና ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ በዛሬው እለት በ72 አመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለቤተሰቦቻቸው እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ይመኛል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.