Fana: At a Speed of Life!

አሲዳማ የሆነ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬትን ለማከም የኖራ እጥረት ተግዳሮት መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሲዳማነት የተጠቃን ሰባት ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማከም የኖራ እጥረት ከፍተኛ ተግዳሮት መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤልያስ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷በአሲዳማነት የተጠቃን መሬት ለማከም በሚኒስቴሩ ስር የሚተዳደሩ 11 የኖራ ፋብሪካዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ ፋብሪካዎች የሚያመርቱት ኖራ ካለው ችግር ስፋት አንጻር በቂ አለመሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

አሁን ላይም በአፈር አሲዳማነት የተጠቃን 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማከም የኖራ እና ማጓጓዣ እጥረት እንቅፋት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ችግሩን  በተወሰነ መልኩ ለማቃለል  በሲዳማ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የኖራ ፋብሪካዎች እየተቋቋሙ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ለኖራ መግዣ 800 ሚሊየን ብር ቢመድብም በሩሲያ-ዩክሬን ግጭት ሳቢያ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ በመናሩ ይህንኑ ብር ባለፈው ዓመት እና ዘንድሮ ማግኘት እንዳልተቻለ አንስተዋል፡፡

ለኖራ መግዣ 30 ሚሊየን ብር ለክልሎች መከፋፈሉን ጠቅሰው÷ ይህም ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ማከም እንዳልቻለ አስረድተዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም ከመንግስት ፋብሪካዎች በተጨማሪ የግል ባለሃብቶች በዘርፉ ተሰማርተው በቂ ምርት እንዲያቀርቡ ለማድረግ ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.