ባለፉት 9 ወራት 2 ሺህ 700 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸው ማለፉ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 29 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 9 ወራት ብቻ 2 ሺህ 700 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸው ማለፉን የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
አገልግሎቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመላ ሀገሪቱ 2 ሺህ 700ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ ፥ 1ጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ንብረት መውደሙን አስታውቋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በ288ሺህ ተሽከርካሪዎች ላይ የዲሲፕሊን እርምጃ ተወስዶ ግማሽ ቢሊየን ብር ለመንግስት ገቢ መደረጉንም ነው የአገልግሎቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጀማል አባሶ በመግለጫቸው ያመላከቱት።
የትራፊክ አደጋ መበራከት ምክንያት በማድረግም ከግንቦት 30 እስከ ሰኔ 25 ቀን 2015 ዓም ሦስተኛ ዙር የንቅናቄ ስራ እና የመንገድ ላይ ቁጥጥር እንደሚደረግ ተገልጿል።
በዋናነት ከፍተኛ ጉዳት በሚደርስባቸው በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ፣በሸገር መውጫ አምስት መንገዶች፣ በአማራ፣ ደቡብ እና ሌሎች ክልሎች ንቅቃቄው እንደሚካሄድ ተመልክቷል።
የህዝብ ትራንስፖርት ማህበራት፣ የመንግስት ተቋማት ጨምሮ በአጠቃላይ ስምሪት የሚሰጡ አካላት የተሽከርካሪዎቹን የቴክኒክ ደህንነት እንዲያረጋግጡም ነው የተጠየቁት፡፡
ንቅናቄው ከፍተኛ ቦታ ይሸፍናል የተባለ ሲሆን ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር፣ ጠጥቶ ማሽከርከር፣ ከታሪፍ በላይ መጫንን ጨምሮ ሌሎች የቁጥጥር ስራዎች እንደሚደረጉም ነው የተነሳው፡፡
በፍቅርተ ከበደ