Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ በኒውክሌር ጦር መሣሪያ ቁጥጥር ጉዳይ ከአሜሪካ ጋር ለመነጋገር በሯ ክፍት መሆኑን አስታወቀች

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 29 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ በኒውክሌር ጦር መሣሪያ ቁጥጥር ጉዳይ ላይ ከአሜሪካ ጋር ለመነጋገር በሯ ክፍት መሆኑን አስታወቀች፡፡

የሀገሪቷ ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ÷ የአሜሪካው የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን በፈረንጆቹ 2026 ከሚያበቃው የስትራቴጂክ ጦር መሣሪያዎች ቅነሳ ሥምምነት በኋላ “አሜሪካ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ለመገደብ በሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከሩሲያ ጋር ለመነጋገር ፍላጎት አላት” ማለታቸውን “አስፈላጊ እና አወንታዊ” ሲሉ ገልጸውታል፡፡

እንደሚታወሰው በፈረንጆቹ የካቲት 2023 በተካሄደው የኒውክሌር የጦር መሣሪያን ለመገደብ በመከረው መድረክ ሩሲያ ተሳትፎዋን በይደር አቆይታዋለች፡፡

አሁን ላይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ÷ “የጄክ ሱሊቫንን ቃል በዲፕሎማሲያዊ ሂደቶች ተደግፎ ወደ እውነተኛ ተግባር ይቀየራል ብለን እናምናለን ፤ ለንግግር ያቀረቡትንም መነሻ ሐሳብ ልንቀበለው እንችላለን” ብለዋል ፡፡

በዚህ ጊዜ እንዲህ ባሉ የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን በተመለከቱ እና እጅግ ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በሚሠጡ መግለጫዎች መተማመን ከባድ እንደሆነም ቃል አቀባዩ ሳያነሱ አላለፉም፡፡

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሜር ፑቲን የካቲት ወር ላይ ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር “የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እና የሩሲያ አቶሚክ ኃይል ኮርፖሬሽን የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ሙከራ ለማድረግ ሁልጊዜም በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው ብለዋል።

ነገር ግን ሙከራውን ለማድረግ ቀዳሚዎች አንሆንም አሜሪካ ካደረገች ግን እኛም እናደርጋለን” ማለታቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን አስታውሶ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.