Fana: At a Speed of Life!

መንግስት ሂዩማን ራይትስ ዎች ያወጣው ሪፖርት ተቀባይነት የለውም አለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት ሂዩማን ራይትስ ዎች ያወጣው ሪፖርት ተቀባይነት እንደሌለው አስታወቀ፡፡

መንግስት ሂዩማን ራይትስ ዎች ያወጣውን ሪፖርት አስመልክቶ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ምላሹም እንደሚከተለው ይቀርባል፡-

ሂዩማን ራይትስ ዎች የተባለው ድርጅት እ.ኤ.አ. ጁን 1 ቀን 2023 (ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም) በሀገራችን በአንዳንድ አካባቢዎች ጉልህ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚገልጽ መሰረተ ቢስ ሪፖርት አውጥቷል ብሏል።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው ግጭት በርካታ አካባቢዎችን ለጉዳት ያጋለጠ ቢሆንም በልዩ ሁኔታ የተወሰነ አካባቢን መርጦ ደጋግሞ ሪፖርት በማዘጋጀት በሰብዓዊ መብት አጀንዳ ሽፋን የተለየ የፖለቲካ ተልዕኮዉን ለማሳካት ዓላማ ያደረገ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም። የመብት ጥሰት ተፈጽሟል ለማለት የቀረበው ሪፖርት ይዘት ሲታይም ተገቢው ምርመራ ያልተደረገበት እና በበቂ ማስረጃ ያልተደገፈ ከመሆኑ አንጻር እምነት የሚጣልበት አይደለም።

በአጠቃላይ በድርጅቱ የቀረበው ሪፖርት የተዛባና በአካባቢው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የማይገልጽ፣ ለዘመናት አብረው የቆዩ ሕዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት የሚያጠለሽ፣ በሕዝቦች መካከል ግጭት ቀስቃሽ የሆነና ሀገራችን እያደረገች ያለውን የእርቅ እና ምክክር ሂደት የሚያደናቅፍ አሉታዊ ተፅዕኖ ያለው ሪፖርት ሆኖ አግኝተነዋል።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው ግጭት በአፋር፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጉዳት ያደረሰ መሆኑ የሚታወቅ ሆኖ ሳለ ድርጅቱ አንድ አከባቢን ለይቶ በመምረጥ ሪፖርት ማውጣቱና ሪፖርቱም ሀገራችን የእርቅ ሂደቱን በተሟላ መልኩ በመተግበር ላይ እያለች በመሆኑ ድርጅቱ ድብቅ አጀንዳውን በሀገራችን ላይ ለማራመድና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተዛባ ዕይታ እንዲኖረው ለማድረግ እየሰራ ለመሆኑ ማሳያ ነው። ሀገራችን ኢትየጵያ የሰብአዊ መብቶችን ለማክበርና ለማስከበር የሚያስችሉ የህግ እና ተቋማዊ አደረጃጀቶች ያሏት ሀገር ስትሆን ይህንኑ ክትትል ለማድረግም እንደ የኢትየጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያሉ ነጻና ገለልተኛ ተቋማትን አቋቁማለች።

መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽሞ የማይታገስ በመሆኑ ምክንያት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ግጭት ተፈጸሙ የተባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት ጥምር የምርመራ ቡድን እንዲያጣሩ አስፈላጊውን ሁኔታ በማመቻቸትና ሪፖርቱም ሲወጣም በሪፖርቱ የተሰጡ ምክረ-ሃሳቦችን ለመተግበር የሚኒስቴሮች ጥምር ግብረ-ኃይል በማቋቋም መጠነሰፊ የሆኑ ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋም፣ ተፈጸሙ የተባሉ የመብቶች ጥሰቶች ምርመራ እና የህግ ማሻሻያ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል።

ከዚህ በተጨማሪም በሰሜኑ ሀገራችን ክፍል የነበረውን ግጭት ለማቆም በፕሪቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ለማስፈጸም ብሎም በሀገራችን የሚታዩ አለመግባበቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ አማራጮችን በማዘጋጀት በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ውይይት እየተደረጉ ይገኛሉ።

የቀረቡ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ አማራጮች ላይ ከመንግስታዊ ተቋማት፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች እና ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ አባላት ጋር ሰፊ ምክክሮችና የግብአት ማሰባሰቢያ ስራዎች ተሰርተዋል፤ እየተሰሩም ይገኛሉ፡፡ የሽግግር ፍትህ ሂደቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የፈጸሙ ወገኖች ላይ ተገቢው ማጣራትን በማድረግ ተጠያቂነትን ማስፈንን ጨምሮ እውነትን የማፈላለግ እና ተጎጂዎችንም መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ማእቀፍ ይፈጥራል። በተጓዳኝ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በሀገራችን የሚታዩ ግጭት እና አለመግባባቶችን ከስር መሰረታቸው በመለየት በዘላቂነት ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

በሀገራችን ያሉ ችግሮችን ከመሰረቱ ለመቅረፍ በራስ አቅም እየተሰሩ ካሉ ስራዎች በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት ጥምር የክትትል ቡድን ተደራጅቶ ግጭቱ በነበረባቸው አካባቢዎች ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል እንዲያደርጉ በመጋበዝ መንግስት በሀላፊነት መንፈስ እየሰራ ባለበት ወቅት ይህንን ከግንዛቤ ሳያስገባ እና በቂ ማስረጃ በሌለበት ከላይ በተጠቀሰው ድርጅት የወጣው ሪፖርት ገንቢ ያልሆነና ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው።

ግንቦት 29 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.