Fana: At a Speed of Life!

ፍርድ ቤቱ ጎበዜ ሲሳይን ጨምሮ  በ7 ግለሰቦች ላይ  የ5 ቀን ክስ የመስረቻ ጊዜ ፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በትናንትናው ዕለት ጎበዜ ሲሳይን ጨምሮ በሽብር ወንጀል በተጠርጠሩ ሰባት ግለሰቦች ላይ የ5 ቀናትየክስ መመስረቻ ጊዜ ለዐቃቤ ኅግ ፈቀደ።

የክስ መመስረቻ ጊዜው የተፈቀደው ዐቃቤ-ኅግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ያቀረበውን የክስ መመስረቻ ጊዜና የተጠርጣሪ ጠበቆችን መከራከሪያ ነጥብ መርምሮ ነው ፡፡

በሌላ በኩል ፣ ፍርድ ቤቱ የፌደራል ፖሊስ መርማሪ የምርመራ ሥራዬን አላጠናቀኩም ባላቸው በሌሎች አራት ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ የሰባት ቀናት የምርመራ ማጠናቀቂያ ጊዜ ለፖሊስ ፈቅዷል።

የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ከዚህ በፊት በሦስት መዝገቦች ተነጣጥለው ምርመራ ሲደረግባቸው በነበሩ የሽብር ወንጀሎች የተጠረጠሩ የ12 ግለሰቦችን ጉዳይ ተመልክቶ ነበር።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ÷ ከ12 ተጠርጣሪዎች መካከል ወንደሰን ተገኝ የተባለ ተጠርጣሪ ላይ የተገኘ ሽጉጥን ተከትሎ የጦር መሣሪያ ኅጋዊነትን በሚመለከት እንዲጣራ ለንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ማስተላለፉን ገልጾ በተጠርጣሪው ላይ ሲታይ የነበረው የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ እንዲዘጋለት ችሎቱ አስታውቋል።

ሌሎችን ተጠርጣሪዎችን ፣ ማለትም ÷ በቀለ ኃይሌ (ዶ/ር) ፣ ጌታቸው ጥዑመልሳን ፣ ሙሉቀን ወንዴ እንዲሁም ጌትነት ወንደሰንን በሚመለከት በተጠረጠሩበት የሽብር ወንጀል የምርመራ ሥራውን አለማጠናቀቁን ገልጿል።

ከዚህ በፊት በተሰጠው የ10 ቀናት የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ውስጥ ሠርቻለሁ ያላቸውን ፣ ማለትም ÷ የተጠርጣሪዎችን ቃል መቀበል ፣ የመኖሪያና የሥራ ቦታቸውን ብርበራ ማከናወን ፣ የቴክኒክ የፎረንሲክ ማስረጃዎችን መቀበሉን እንዲሁም የምስክር ቃል መቀበሉን አስረድቷል።

ቀረኝ ያላቸውን ቀሪ የምስክር ቃል የመቀበል ፣ የቴክኒክ እና የፎረንሲክ ማስረጃዎችን የማስተንተን እንዲሁም ሌሎች ማስረጃዎችን የመሰብሰብ ሥራ እንደሚቀረው ጠቅሶ ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

በተጠርጣሪ ጠበቆች በኩል ደግሞ ÷ በፖሊስ የተጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ማጠናቀቂያ ጊዜ ጥያቄ የኅግ አግባብ የሌለው መሆኑን ጠቅሰው ተከራክረዋል።

በተጨማሪም ጠበቆቹ ፖሊስ ምርመራውን እያሰፋ ከወንጀለኛ ሥነ-ሥርዓት ኅግ ቁጥር 59 ውጪ ተጠርጣሪዎችን በእስር ለማቆየት የሚያደርገውን ድርጊት ፍርድ ቤቱ ክትትል ሊያደርግበትና የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄውን ሊገድብ ይገባል በማለት የመከራከሪያ ነጥባቸውን አንስተዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ÷ አዲስ የምርመራ ሥራ አልተከናወነም የሚለውን የጠበቆች መከራከሪያ ነጥብ በሚመለከት፥ ፖሊስ በተሰጠው የ10 ቀናት ጊዜ ውስጥ በርካታ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን ጠቅሶ ማብራሪያ ሰጥቷል።

የምርመራ ቡድኑ ጉዳት በደረሰባቸው ቦታዎች ላይ የምስክር ቃልና ማስረጃ እየሰበሰበ መሆኑን በመጥቀስም የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ በመቃወም ተከራክሯል።

ክርክሩን የተከታተለው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ÷ መዝገቡን መርምሮ ከቀሪ የምርመራ ሥራ እና ከወንጀሉ ልዩ ባህሪ አንጻር ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ቀሪ ማስረጃ የማሰባሰብ ሥራ ሊደናቀፍ ይችላል የሚል ዕምነት በመያዝ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ በማለፍ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ የሰባት ቀናት የምርመራ ማጠናቀቂያ ጊዜ ፈቅዷል።

በሌላ በኩል በበሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በፌደራል ፖሊስ የፀረ-ሽብር ምርመራ ዘርፍ ÷ ምርመራ ሲከናወንባቸው የቆዩ ሰባት ተጠርጣሪዎች ማለትም ÷ ጎበዜ ሲሳይ ፣ ዮርዳኖስ አለሜ ፣ ተሥፋዬ መኩሪያ ፣ ጌታወይ አለሙ ፣ ሐብታሙ ዳኜ ፣ ታደሰ ወንዳይነው እንዲሁም ጌታቸው ወርቄን በሚመለከት ፖሊስ የምርመራ ሥራውን ማጠናቀቁን እና መዝገቡን ለዐቃቤ ኅግ ማስረከቡን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስታውቋል።

በመዝገቡ ላይ የተሰየመው የተደራጁና የድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤኅግ ÷ በተጠርጣሪዎች ላይ ከፖሊስ የተረከብኩትን መዝገብ ተመልክቼ ክስ ለመመስረት እንዲያስችለኝ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ኅጉ 109/ንዑስ ቁጥር 1መሠረት የአምስት ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ እስከዚያው በማረፊያ ቤት ይቆዩና ክስ ከተመሰረተ በኋላ በዋስትናው ላይ ክርክር ይካሄድ የሚል ጥያቄም አንስቷል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ÷ ዐቃቤ ኅግ ምርመራውን ሲመራ ቆይቶ አሁን ለክስ መመስረቻ ጊዜ መጠየቁ አግባብ አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል።

በተለይም ችሎቱ ሥልጣኑ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ኅግ ቁጥር 59 መሰረት በሂደት ላይ ያለ ጊዜ ቀጠሮ ላይ ነው እንጂ ተጠርጣሪዎች ክስ እስከሚመሰረት በእስር እንዲቆዩ የሚያደርግበት ሥልጣን የለውም የሚሉ ፍሬ ነገሮችን አንስተው ተከራክረዋል።

በተጨማሪም ጠበቆቹ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ኅግ ቁጥር 109 ለዐቃቤ-ኅግ በሚጠቅም መልኩ ሊተረጎም አይገባም ያሉ ሲሆን ፍርድ ቤቱ የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን ዘግቶ ተጠርጣሪዎቹን እንዲያሰናብትላቸው ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ኅግ በበኩሉ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ኅግ ቁጥር 59 መሰረት የጊዜ ቀጠሮ ምርመራ መዝገቡ በሚዘጋበት መሃል ገደብ የሌለው በመሆኑ መዝገቡን በማየት የተጠርጣሪዎችን አቆያየት ላይ ፍርድ ቤቱ እየተከታተለ እንዲወስን በማስፈለጉ ምክንያት በወ/መ/ስ/ህ/ቁጥር 109 መሰረት ጥያቄዎችን ተቀብሎ ፍርድ ቤቱ እንደሚያስተናግድ ገልጾ ማብራሪያ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ ሥልጣን የለውም የሚለው የጠበቆችን መከራከሪያ በሚመለከት በመዝገቦቹ ላይ መርምሮ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን ያለው ፍርድ ቤቱ መሆኑን ጠቅሶ ዐቃቤ ኅግ መልስ ሰጥቷል።

እንደ አጠቃላይ በጠበቆች የተነሳው የዋስትና ጥያቄን በሚመለከት በቡድን የተፈጸመ የሽብር ወንጀል ድርጊትና የሰው ሕይወት የጠፋበት መዝገብ መሆኑን በመጥቀስ ዐቃቤ-ኅግ ተጠርጣሪዎቹ በውጭ ግብረ-አበሮች ያላቸው በመሆኑ ቢወጡ ላናገኛቸው እንችላለን በማለት ስጋቱን ገልጾ የዋስትና ጥያቄያቸውን ተቃውሟል።

ክርክሩን በይደር የመረመረው ችሎቱ ÷ ተጠርጣሪዎች ክስ እስከሚመሰረትባቸው ድረስ በማረፊያ እንዲቆዩ ፍርድ ቤቱ የመወሰን ሥልጣን የለውም ተብሎ በጠበቆች የተደረገውን ክርክር በሚመለከት ተጠርጣሪዎች ክስ እስከሚመሰረትባቸው በማረፊያ ቤት እንዲቆዩ የመወሰን ሥልጣን ፍርድ ቤቱ እንዳለው ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

እንደ አጠቃላይ የተጠረጠሩበት ወንጀል የሰው ሕይወት የጠፋበት የሽብር ወንጀል መሆኑ ተጠቅሶ የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገ ሲሆን ለዐቃቤኀግ የ5 ቀናት ክስ የመመስረቻ ጊዜ ተፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.