የሀገር ውስጥ ዜና

ማይክ ሐመር እና ትሬሲ አን ጃኮብሰን በኢትዮጵያ ከአፍሪካ ኅብረት የሠላም ሂደት ክትትል ቡድን ጋር ተወያዩ

By Alemayehu Geremew

June 07, 2023

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን የአፍሪካ ኅብረት በኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከመደባቸው የሠላም ሂደት ክትትል ቡድን ጋር ተወያይተዋል።

ቡድኑ በመቀሌ የሠላም ሂደቱን የመከታተል ፣ የማረጋገጥ እና ቅሬታ የመሥማት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ግጭት የተከሰተበት የሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል ሠላም ወደ ነበረበት እንዲመለስ ቡድኑን ሲመሩ የቆዩት ሜጀር ጀነራል ስቴፈን ራዲናንም በአዲስ አበባ አግኝተዋቸው መምከራቸውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡

ዘላቂ ሠላም በቀጣናው እንዲሰፍን የአፍሪካ ኅብረት ያቋቋመው ቡድን እየተወጣ ያለውን ሚና አድንቀው ሥልጣኑም እስከ ሚቀጥለው ታኅሣሥ ወር ቢራዘም ደስተኞች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡