በሰሜን ሸዋ ዞን የበቆሎና ማሽላ ሰብሎች ላይ ተምች ተከሰተ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአመራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የበቆሎና ማሽላ ሰብሎች ላይ ተምች መከሰቱ ተገለፀ።
ተምቹ በዞኑ ሦስት ወረዳዎች ላይ መከሰቱን የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ገልጿል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ አበበ ጌታቸው ፥ 4 ሺህ 132 ሄክታር ማሳ ላይ የአፍሪካ ተምች ተከስቷል ብለዋል፡፡
ሆኖም 2 ሺህ 745 ሄክታሩ የኬሚካል ርጭት እንደተደረገበትም ነው የገለጹት።
በዚህም 3 ሺህ 508 ሊትር ኬሚካል ጥቅም ላይ እንደዋለ የገለፁት ቡድን መሪው ፥ ቀሪው ማሳ ላይ የኬሚካል እጥረት በመፈጠሩ ርጭት አለመደረጉን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ የኬሚካል አቅርቦቱ እንደተዳረሰ ማሳዎቹ ላይ የኬሚካል ርጭት እንደሚደረግም ነው ያነሱት፡፡
ወቅቱ ለተባይ ስርጭት ምቹ በመሆኑ አርሶ አደሩ የማሳ ቅኝት በማድረግ የተባይ ስርጭቱን መከላከል እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
በኤልያስ ሹምዬ