Fana: At a Speed of Life!

የካራማራው ጀግና ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈጸመ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የካራማራው ጀግና ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ቀብር ሥነ-ሥርዓት በዛሬው ዕለት በቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡

በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ወዳጅ ዘመዶቻቸው  ተገኝተዋል፡፡

ሻለቃ ባሻ አሊ በርኬ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም በ72 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል፡፡

የቀድሞው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል የነበሩት ጀግናው አሊ በርኬ ፥ እናት ሀገር ተወራለች ዝመት በተባሉበት የልጅነት ዕድሜያቸው የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር እና ወራሪውን የዚያድባሬን ጦር ለመመከት ከእኩዮቻቸው ጋር ዘምተዋል።

የሶማሊያው ዚያድባሬ ጦር እስከ አፍንጫው ታጥቆ የመስፋፋት ህልሙን ለማሳካት ኢትዮጵያን ሲወር፥ አሊ በርኬ እና ጓደኞቻቸው ግንባር በመዝመት ምንጊዜም የሚታወሰውን የካራማራ ጦርነት በድል ተወጥተዋል።

በወቅቱ የዚያድባሬን ወረራ ለመመከት የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም፥ ሚያዚያ 4 ቀን 1969 ዓ.ም የእናት ሀገር አድን ጥሪን አውጀው ነበር።

ጀግናው ሻለቃ አሊ በርኬም ጥሪውን በመቀበል ከቀድሞው ወለጋ ክፍለ ሀገር አሶሳ አውራጃ ቤጊ ወረዳ  ወደ ኦጋዴን ዘምተዋል።

በዚህም በኦጋዴን አቡሸሪፍ ግንባር በተደረገ ከባድ ውጊያ የወራሪውን የሶማሊያ ሀይል ቲ-55 ታንኮች በእጅ ቦምብ ደጋግመው በማጋየት ማርከው ትልቅ ጀብድ ሰርተዋል።

በዚህ ጦርነት ኢትዮጵያ በእነ አሊ በርኬና ሌሎች ጀግና ኢትዮጵያውያን ታላቅ ተጋድሎ በታላቁ የካራማራ ድል ሉዓላዊነቷን አስከብራ ቆይታለች፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.