Fana: At a Speed of Life!

ከአውስትራሊያ ጋር በክህሎት ልማት እና በሥራ ዕድል ፈጠራ በጋራ መስራት በሚቻልበት አግባብ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 30 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአውስትራሊያ ጋር በክህሎት ልማት እና በሥራ ዕድል ፈጠራ በጋራ መስራት በሚቻልበት አግባብ ላይ ተወያየ።

 

በዚህ ወቅት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በኢትዮጵያ በኩል የሰለጠነ እና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል ለሥራ ማሰማራትን በተመለከተ በኢትዮጵያ ለአውስትራሊያ አምባሳደር ጁሊያ ኔብሌት አብራርተውላቸዋል።

 

በማብራሪያቸውም ከኢትዮጵያ ህዝብ 70 ከመቶ ያህሉ ዕድሜው ከ30 ዓመት በታች መሆኑን በመጥቀስ፥ ለሥራ ዝግጁ ለሆነው ወጣት ኃይል የሥራ ዕድል መፍጠር የመንግስት አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።

 

ከተለያዩ ሀገራት ጋር ስምምነት በመፈፀም በተለያዩ ሙያዎች የሰለጠነ እና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማሰማራት ጥረት መደረጉንም አንስተዋል።

 

ከዚህ ቀደም በአውስትራሊያ ኤምባሲ ዕገዛ በአፍሪካ ነፃ ቀጣና ዕድል እና ዓለም አቀፍ ገበያን መጠቀምን በተመለከተ ለኢንተርፕራይዞች ስልጠና መሰጠቱን በማንሳትም፥ ከዚህ ቀደም የተሰጠውን ስልጠና ለማስፋት ውይይት መጀመሩ መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

 

የሰለጠነ እና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይል ለሥራ ማሰማራት፣ በተለዩ ዘርፎች የቴክኒክና ሙያ ስልጠና መስጠት፣ የኢንተርፕራይዞች ዕድገት፣ የኢትዮጵያ ብየዳ ማዕከል ስልጠና ማስፋት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

 

በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር ጁሊያ ኔብሌት በበኩላቸው በነርሲንግ፣ በማምረቻ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን እና ሌሎችም ዘርፎች የአውስትራሊያን ወቅታዊ ኢኮኖሚ መሠረት ያደረጉ የሥራ ዕድሎችን ለኢትዮጵያውያን ለመፍጠር  ውይይቱ ይቀጥላል ብለዋል።

 

ብቁ እና የሥራ ልምድ ያለው የሰው ኃይል ለማሰማራት ከመፈለግ ባሻገር በተለያዩ የስልጠና ዘርፎች እና የዕውቀት ሽግግር ላይ በጋራ ለመስራት ውይይቶቹ መጀመራቸውን አድንቀዋል።

 

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከአውስትራሊያ ጋር የልማት እና የትብብር ስምምነቶችን መፈረሟ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በጋራ ለመስራት ለተጀመረው ውይይት መልካም አጋጣሚ መሆኑም በዚህ ወቅት ተነስቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.