Fana: At a Speed of Life!

አልሸባብ ሊፈፅም የሞከረው የጥፋት ሴራ በመከላከያ ሠራዊቱ ጥንካሬ ሙሉ በሙሉ መክሸፉን የመከላከያ ሰራዊት ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አልሸባብ ሊፈፅም የሞከረው የጥፋት ሴራ በመከላከያ ሠራዊቱ ጥንካሬ ሙሉ በሙሉ መክሸፉን የመከላከያ ሰራዊት ገለጸ።

አልሸባብ በተለያየ ጊዜ በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ስጋት ለመፍጠር የጥፋት ሙከራዎችን ቢያደርግም በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ሴራው እየከሸፈ የሽብር ቡድኑም መደምሰሱ ተገልጿል፡፡

ከሰሞኑም አልሸባብ በኢትዮጵያ ሶማሊያ ድንበር ዶሎ ካምባስ በተባለ ቦታ በሁለት መኪና ፀረ ሰውና ፀረ ተሽከርካሪ ፈንጅዎችን ጭኖ በሠራዊቱ ላይ ጉዳት ለማድረስ ቢሞክርም በጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ሁለት መኪናዎች እና ስድስት አሸባሪዎች ከእነ ፈንጅዎቻቸው ዶግ አመድ መሆናቸውን ኮሎኔል ፈይሳ አየለ ተናግረዋል።

አልሸባብ በሁለት መኪና ሙሉ ፈንጅ ጭኖ በሠራዊታችን ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ኬላን በጥሶ ለማለፍ ቢሞክርም በጥበቃ ቦታ ላይ የነበሩት ጀግኖች የመከላከያ ሠራዊት አባላት የጠላት መኪና መሆኑን ቀድመው በመረዳት አባላቱ በታጠቁት መሳሪያ አውድመውታልም ተብሏል።

በመሆኑም አልሸባብ ድል እቀዳጅበታለሁ ብሎ ያሴረው ሴራ በጀግኖች የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከሽፎበታልም ነው የተባለው።

የክፍለ ጦሩ ህብረት ዘመቻ ሃላፊ ሻለቃ መሃመድ ሮብሌ በቦታው ላይ በመገኘት አልሸባብ በሠራዊቱ ላይ የተለያዩ ትንኮሳዎችን ለመፈፀም ቢሞክርም ቀደምትነትን በመውሰድ የአልሸባብን ሴራ እና ተንኮል እያከሸፉ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

ምንጊዜም የጥንቃቄ ስልቶችን በመከተል ከአካባቢው የፀጥታ ሃይል እና ከሲቪል ህብረተሠቡ ጋር ተቀናጅተን በመሥራታችን ውጤታማ ሆነናልም ብለዋል።

ሻለቃ መሃመድ ሁለቱ ጓዶች ማለትም 50 አለቃ ብሩክ ደበበ እና መሰረታዊ ወታደር ጀማል ሰይድ የአልሸባብን ሴራ በማክሸፍ የሰሩት ጀብድ ኢትዮጵያዊነት ጀግንነት መሆኑን ያረጋገጠ ነው ሲሉ መግለጻቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.