በግሪክ የኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ላይ ምርመራ መጀመሩን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በግሪክ የኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ላይ በወንጀል ጥርጣሬ በደረሰ ጥቆማ ምርመራ መጀመሩን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ፍትሕ ሚኒስቴር የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ቦርድና አስተዳደር ከተለያዩ ወንጀሎች ጋር ተያይዞ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በደረሰ ጥቆማ መሰረት የወንጀል ምርመራ መጀመሩን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
በዘርፉ በወንጀል የተገኘ ኃብት ምርመራና ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጄነራል ዳይሬክተር ጸጋ ዋቅጅራ እንደገለጹት ÷ ምርመራው የተጀመረው የቀድሞ ቦርድና አስተዳደር በወንጀል ድርጊት ተሳትፈዋል በሚል በመጠርጠራቸው ነው።
የተለያዩ የወንጀል ጥርጣሬዎች መኖራቸውን የገለጹት ጄኔራል ዳይሬክተሩ÷ከዚህ መካከል በወንጀል የተገኘ ኃብት እንዳይሸሽ ለማድረግ ትኩረት መደረጉን ጠቁመዋል።
አዲስ የተሾመው አስተዳደር በሙስና ወንጀል ልዩ ሥነ-ሥርዓት ሕግ 434/1993 አዋጅ መሰረት ለፍትሕ ሚኒስቴርና ለፖሊስ በተሰጠ ሥልጣን መሰረት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የተሾሙት አስተዳዳሪዎች ንብረቱን በጊዜያዊነት ተረክበው የወንጀል ክስና ምርመራው ተጠናቆ የመጨረሻ ውሳኔ በመዝገቡ እስከሚገኝ ድረስ ንብረት እንዲጠብቁና እንዲያስተዳድሩ መሾማቸውን ነው ያስረዱት።
አስተዳዳሪዎቹ ንብረቶቹን ከማስተዳደር ባሻገር የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዳይስተጓጎል ትምህርት ቤቱን እንዲመሩ ከቀድሞ የትምህርት ቤቱ ቦርድ ሥራ መረከባቸውንም ገልጸዋል።
ለግሪክ ትምህርት ቤት ጊዜያዊ አስተዳደር ሆነው ከተሾሙት መካከል ጌታቸው ተፈራ፥ አዲሱ አስተዳደር ከትናንት ጀምሮ ስራ መጀመራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡