በአዲስ አበባ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር 17 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር 17 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ማድረጉን የከተማዋ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ይመኙሻል ታደሰ እንዳሉት÷ በሁለተኛው ምዕራፍ 17 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ከ2 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎችን በማሳተፍ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች የጉድጓድ ቁፋሮ እየተከናወነ ነው።
ከሚተከሉት ችግኞች መካከል 20 በመቶ የፍራፍሬ፣ 20 በመቶ የውበት ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ የጥላ ዛፎች መሆናቸውን አብራርተዋል።
በመጀመሪያው ዙር መርሐ ግብር የተተከሉት ችግኞች ተገቢው ጥበቃና እንክብካቤ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰው የጽድቀት መጠን 86 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዘንድሮው የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ስኬት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣና የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦችም ችግኞችን እንዲተክሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በመዲናዋ ባለፉት አራት ዓመታት 41 ሚሊየን ችግኞች መተከላቸውን ኢዜአ በዘገባው አስታውሷል።