ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሐዋሳ ከተማ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ተወካዮች ጋር እየተወያየ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሐዋሳ ከተማ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ተወካዮች ጋር እየተወያየ ነው፡፡
ምክክሩ በሀገር ደረጃ ውክልና ወስደው በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ውስጥ ሊሳተፉ የሚችሉ ሶስት ሠዎችን ለመምረጥ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)÷የሚመረጡት ግለሰቦች የማህበረሰቡን ችግር በቅጡ የተረዱና ማስረዳት የሚችሉ መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ማንም ሰው ከህሊናው አያመልጥም ያሉት ኮሚሽነሩ÷ ህዝብን የሚወክሉ ሰዎች በፖለቲካና ሌሎችም አሉታዊ ሀሳቦች እውነትን የማይለውጡ መሆን አለባቸወ ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የኢትዮጵያ አንድነትና የህዝቦቿ ሰላም የሚገዳቸውና ለዚያም ዋጋ ለመክፈል የማይሰስቱ መሆን ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ኮሚሽነር ዮናስ የኢትዮጵያን አንድነት ለማፅናት ከመቼውም ጊዜ በላይ ሁሉም ያለመታከት ሊሰራ ይገባል፤ ያኔ የምንፈልጋትን ትልቅ ሀገር መገንባት እንችላለን ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በምክክር ጉባዔው የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ የሁሉም ማህበረሰብ ክፍሎች ከሐዋሳ ከተማ ስምንት ክፍለ ከተሞች በአጠቃላይ 3 ሺህ 600 ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
በማህሌት ተ/ብርሃን