ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ሙስና በመቀበል በተጠረጠሩ የከተማ አስተዳደሩ ሰራተኞች ላይ ክስ ተመሰረተ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 1 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባዶ መሬት እናሰጣለን በሚል ሀሰተኛ ሰነድ አዘጋጅተው ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ሙስና ተቀብለዋል የተባሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ሶስት ሰራተኞች ላይ ክስ ተመሰረተ፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ አምስት ተደራራቢ የማታለል የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።
ክሱ የተመሰረተው በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3 ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሾቹ 1ኛ የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የግንባታ ቁጥጥር ባለሙያ ፍቅረስላሴ ታደለ፣ 2ኛ የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤት ቅሬታ ሰሚ ዳይሬክተር ታምራት እስጢፋኖስ እና የየካ ክፍለ ከተማ መሬት አስተዳደር የመብት ፈጠራ ቡድን መሪ ዘውዱ ደገፋ ናቸው።
በክሱ ላይ እንደተመላከተው 1ኛ ተከሳሽ የዐቃቢ ሕግ ምስክር የሆኑ የግል ተበዳይን በማግኘት እራሱን የከተማ አስተዳድሩ የመሬት አስተዳደር ካቢኔነኝ ብሎ ተበዳይን በማሳመን፣ ግለሰቡን በጥቅምት 2 ቀን 2015 ዓ.ም በአራዳ ክ/ከተማ ወረዳ 05 ከንቲባ ጽ/ቤት ቅጥር ጊቢ በመጥራት ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 አራራት ሆቴል ጀርባ 5 ሺህ ካሬ ሜትር ባዶ ቦታ እንሰጣለን በማለት አስቀድመው 25 ሚሊየን ብር ሙስና ገንዘብ ከጠየቁ በኋላ በቅድሚያ ለፕሮጀክት ማሰሪያ 250 ሺህ ብር በቼክ መቀበላቸው በክሱ ተጠቅሷል።
በጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም ደግሞ የግል ተበዳዩ የኗሪነት መታወቂያ ኮፒ፣ ፓስፖርት ኮፒ፣ የባንክ ስቴትመንታቸውን ኮፒ ሰነዶችን እንዲሰጧቸው በማድረግ በጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም 2 ሚሊየን ብር በቼክ መቀበላቸው በክሱ ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ከሁለቱ ከግል ተበዳዮች 10 ሚሊየን 250 ሺህ ብር መቀበላቸውን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ አብራርቷል።
በተጨማሪም 1ኛ እና 2ኛ ተጠርጣሪ የሜሪዲያን ሆቴል ባለቤት ለሆኑት ግለሰብ በሆቴሉ ስም የተመዘገበ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የመከነ ቢሆንም በይዞታው ላይ ጭማሪ ካሬ ሜትር በማካተትና የመከነውን ካርታ እንደሚስተካከልላቸው በመግለጽ የተለያዩ የከተማ አስተዳደሩ ሀሰተኛ ሰነዶችን ለግል ተበዳይ ማሳየታቸውን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል።
በዚህ መልኩ ሀሰተኛ የከተማ አስተዳደሩ ሰነዶችን በ1ኛ ተጠርጣሪ መኖሪያ ቤትና በ2ኛ ተጠርጣሪ በሚያሽከረክረው መኪና ውስጥ በብርበራ መገኘቱ በክሱ ተጠቅሷል።
በዚህ መልኩ በ1996 ዓ/ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 1 ሀ እና ለ የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 32 ንዑስ አንቀጽ 2 የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ተደራራቢ የማታለል የሙስናወንጀል ክስ ቀርቧባቸዋል።
ተከሳሾቹ በዛሬው ቀጠሮ ክሱ ከደረሳቸው በኋላ የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ÷ የተከሰሱበት አንቀጽ ዋስትና እንደማያስፈቅድ ጠቅሶ የተከራከረሲሆን ፍርድ ቤቱ መርምሮ የዋስትና ጥያቄያቸውን ውድቅ በማድረግ ወደ አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ አዟል።
ተከሳሾች የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለሰኔ 6 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ