Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ 801 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ሆኖ በቀረበው የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር ዕይታ መራ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 801 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ሆኖ በቀረበለት የ2016 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቶ ለዝርዝር ዕይታ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 24ኛ መደበኛ ስብሰባ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡

ረቂቅ በጀቱ  ለምክር ቤቱ የቀረበ ሲሆን፥ በረቂቅ በጀቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው በቀጣዩ ዓመት የተያዘው አቅድ በከፍተኛ ጥንቃቄ መዘጋጀቱን ጠቁመው÷በተለይም የዋጋ መረጋጋትን እንደ ትልቅ ግብ የያዘ እቅድ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ረቂቅ በጀቱ በእቅድ የተያዙ  የልማት ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል ታሳቢ አድረጎ መዘጋጀቱን የገለጹት ሚኒስትሩ ÷ በአጠቃላይ የገቢ አቅምን ማሳደግ እንደሚያስችልም አስረድተዋል፡፡

የውጭ ምንዛሬ ዕጥረትን ለመቋቋም፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንዲሁም የግል ሴክተሩን ሚና ማሳደግ በሚያስችል ሁኔታ በትኩረት መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 21ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2016 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ የበጀት አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡

የ2016 በጀት በአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ታሳቢ በማድረግ፣ የሀገር ደህንነት ከማስጠበቅ፣ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጐችን ከመርዳት፣ በህግ ማስከበር ዘመቻው የወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሶ ከማቋቋም፣ በቀጣይ ሊኖር የሚችለውን የማህበራዊና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አቅጣጫዎችና ዓላማዎች ከማሳካት አኳያ የተቃኘ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ረቂቅ በጀቱ የ2016 – 2020 የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚ እና የፊሲካል ማዕቀፍን መሠረት በማድረግ ተዘጋጅቶ የቀረበ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

በዚሁ መሰረት ለፌደራል መንግስት መደበኛ ወጪዎች ብር 369 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር፣ ለካፒታል ወጪዎች ብር 203 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ ብር 214 ነጥብ 07 ቢሊየን ብር፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ 14 ቢሊየን ብር በጠቅላላው 801 ነጥብ 65 ቢሊየን ብር ሆኖ ነው  ለምክር ቤቱ የቀረበው፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በረቂቅ በጀቱ ላይ ከተወያየ በኋላ ለዝርዝር እይታ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.