Fana: At a Speed of Life!

የአፋር ክልል ግብርናን ለማሻገር ስራዎች በሕዝብ ንቅናቄ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፋር ክልል ግብርናን ለማሻገር የሚያግዝ ረቂቅ ፍኖተ-ካርታ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ (ኢ/ር) ፣ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

በረቂቅ ፍኖተ-ካርታው የእንስሳት፣ የሰብል፣ የተፈጥሮ ሃብት፣ የመስኖ እና የግብርና ሜካናይዜሽን ልማት እና የግብርና ምርቶች ገበያ ጉዳዮች መካተታቸው ተጠቁሟል፡፡

ከዚህ ባለፈም በክልሉ ያሉ አቅሞች፣ ተስፋዎች እና በተለዩ ችግሮች ላይ የመፍትሄ ሃሳቦችን የሚያስቃኙ ጉዳዮች በረቂቁ መካተታቸው በመድረኩ ተገልጿል፡፡

ከኢንቨስትመንት መሬት ፣ ከመስኖ ውሃ አጠቃቀም እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ከተሳታፊዎች አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስቶ ውይይት እንደተደረገባቸው የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

አቶ አወል የክልሉን የግብርና ዘርፍ ለማሻገር በክልሉ ያለውን አቅም አንስተው÷ ፍኖተ-ካርታውን ዕውን ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና በመውሰድ ወደ ስራ እንዲገቡ አሳስበዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ማንኛውም የግብርና ስራ ከፍኖተ-ካርታው ጋር የተናበበ ሊሆን እንደሚገባና ፍኖተ- ካርታውን ለማሳካት የህዝብ ንቅናቴ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አይሻ መሃመድ (ኢ/ር)፥ አፋር ክልል ያለውን ሃብት በአግባቡ ከተጠቀመ ዘርፉን በቀላሉ መቀየር እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.