በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተገኙ አመርቂ ውጤቶችን በ2ኛው ምዕራፍ ለመድገም በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ገለጹ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተገኙ አመርቂ ውጤቶችን በሁለተኛው ምዕራፍ ለመድገም በተለይ በጥምር ግብርና ላይ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ገልጸዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ላይ ተገኝተው አሻራቸውን ያሳረፉ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች በሰጡት አስተያየት÷ ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በየክልሎቹ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ የተገኙ ስኬቶችን ለመድገም በቂ ዝግጅት መደረጉን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገልጸዋል።
ክልሉ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የደን፣ የቡና እና የፍራፍሬ ወይም ጥምር ግብርና ስርዓትን በመከተል እንደሚያለማ ተናግረዋል።
በክልሉ ከሚተከሉ አጠቃላይ ችግኞች መካከል 1 ነጥብ 3 ቢሊየን የቡና፣ 50 ሚሊየን ደግሞ የፍራፍሬ ዝርያዎች ተከላ ቀደም ብሎ መጀመሩን ጠቁመዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው÷ ከዕቅድ በላይ ማሳካት በተቻለበት በመጀመሪያው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶች መምጣታቸውን ነው የተናገሩት።
ክልሉ የአየር ንብረት መዛባት ተጽዕኖን የሚቋቋሙ ብቻ ሳይሆን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ችግኞችን ለመትከል ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁንም ገልጸዋል።
በተያዘው የክረምት ወቅት ከሚተከሉ ችግኞች ባሻገር ለቀጣይ ዓመት የሚሆኑ ችግኞችን የማፍላት ስራዎች እንደሚከናወኑም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የህብረተሰቡ ችግኝ የመትከልና የመንከባከብ ባህል መዳበሩን ጠቅሰው÷ በቀጣይ በተለይም ጥምር ደንን ታሳቢ ያደረጉ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ ÷ ትግራይ ክልል በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች አርዓያነት እንደነበረው አስታውሰው፣ ሆኖም በጦርነቱ የተፈጥሮ ሃብት ስራው መስተጓጎሉን አንስተዋል።
በዚህም የተስተጓጎለውን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ለማካካስ በሁለተኛው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በስፋት ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት እንደተደረገ መናገራቸውን ኢዘኤ ዘግቧል።
በተመሳሳይ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦድሪን በድሪ÷ ለምግብነት በሚውሉ ችግኞች ላይ በማተኮር በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
ርዕሳነ መስተዳድሮቹ ሁለተኛው ምዕራፍ በይፋ በተጀመረበት አፋር ክልል የተመለከቱት እምርታ ያመጣ የፍራፍሬ ልማት፤ ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ አቅም የሚያሳይ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም በቆላማ አካባቢዎች ላይ የአመራር ቁርጠኝነት ከተጨመረበት የአየር ንብረት መዛባት ተጽዕኖን መቀነስ ብቻ ሳይሆን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚቻል ጉልህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።