Fana: At a Speed of Life!

“ሣፋሪኮም ኢትዮጵያ” ዓለም አቀፍ ብድር እና ዋስትና ተፈቀደለት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ሣፋሪኮም በኢትዮጵያ እያከናወነ ያለውን የቴሌኮሙኒኬሽን መስመር ዝርጋታ እና ሥራ ለመደገፍ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ኮርፖሬሽን እና ሁለገብ የኢንቨስትመንት አማራጮች ዋስትና ኤጀንሲ ብድር እና ዋስትና መፍቀዳቸውን አስታወቁ፡፡

በዚህም ዓለም አቀፉ የገንዘብ ኮርፖሬሽን በዓለም አቀፍ አጋርነት የ157 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር መዋዕለ-ንዋይ በማቅረብ ከሳፋሪኮም ጋር የሚሰራ ሲሆን፥ የ100 ሚሊየን ዶላር ደግሞ በብድር መልክ ለሣፋሪኮም ኢትዮጵያ ያመቻቻል፡፡

በስምምነቱ መሰረት ዓለም አቀፉ የገንዘብ ኮርፖሬሽን በሣፋሪኮም ኢትዮጵያ የመሪነት ቦታ እንደማይዝም ተመላክቷል።

ሁለገብ የኢንቨስትመንት አማራጮች ዋስትና ኤጀንሲ የተሰኘው ዓለምአቀፍ የዓለም ባንክ ቡድን አባል ደግሞ ÷ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ባለድርሻ ለሆኑት ቮዳፎን ግሩፕ፣ ቮዳኮም ፣ ሳፋሪኮም እና ብሪቲሽ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት የ10 አመት የ1 ቢሊየን ዶላር ዋስትና ይሠጣል ተብሏል፡፡

አበዳሪዎቹ ለ”ሣፋሪኮም ኢትዮጵያ” የብድር እና የዋስትና አገልግሎት የፈቀዱት ለዜጎች እና ለንግድ ተቋማት በተመጣጣኝ ዋጋ የኢንተርኔት እና አስተማማኝ የሞባይል ሥልክ ግንኙነት ለማዳረስ የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ መሆኑ ተመላክቷል።

በሣፋሪኮም እና በባለድርሻዎቹ ቮዳፎን ፣ ቮዳኮም ፣ ብሪቲሽ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት እንዲሁም በሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን እና በአበዳሪዎች መካከል የተመሠረተው ይህ የመጀመሪያ አጋርነት፥ ዓለም ባንክ አዳጊ ሀገራት ድኅነትን እንዲያስወግዱ እና ዜጎቻቸው የተሻለ የዲጂታል ቴክኒሎጅ የመጠቀም ፍላጎታቸውን እንዲያሟሉ ያስቀመጠውን ተልዕኮ የሚያግዝ መሆኑም ነው የተጠቀሰው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.