የሀገር ውስጥ ዜና

በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ ሲደረግባቸው ለቆዩ 4 ግለሰቦች የዋስትና መብት ተፈቀደ

By Alemayehu Geremew

June 09, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ምርመራ ሲደረግባቸው የቆዩ አራት ግለሰቦች የዋስትና መብት ተፈቀደላቸው።

የዋስትና መብት የተፈቀደላቸው ግለሰቦችም ÷ ቴድሮስ አስፋው ፣ ሳሮን ቀባው ፣ ጌታቸው ወርቄ እና ጌታዎይ አለሙ ናቸው።

የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ-ኅግ ÷ በተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ የቀጠለ ቢሆንም ዋስትና ቢፈቀድላቸው እንደማይቃወም አመልክቷል።

በዚህም መሠረት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ÷ ለሳሮን ቀባው የ3 ሺህ ብር ፣ ለቴድሮስ አስፋው የ15 ሺህ ብር እንዲሁም ጌታቸው ወርቄ እና ጌታዎይ አለሙ እያንዳንዳቸው የ10 ሺህ ብር ዋስ አስይዘው ከእሥር እንዲፈቱ አዝዟል።

ዐቃቤ-ኅግ በአጠቃላይ 51 በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ክስ የመሰረተ ሲሆን ÷ 24 ተጠርጣሪዎች ላይ ባሉበት፤ በቀሪዎቹ 27 ተጠርጣሪዎች ላይ ደግሞ በሌሉበት ነው ክስ የመሰረተባቸው።

በታሪክ አዱኛ