የኢትዮጵያ እና ቻይና የሁለትዮሽ ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል – የቻይና ኤምባሲ አማካሪ ሚኒስትር
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት አስር ዓመታት የኢትዮጵያ እና ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት በበርካታ የትብብር ዘርፎች ላይ በፍጥነት እያደገ መሆኑን በኢትዮጰያ የቻይና ኤምባሲ አማካሪ ሚኒስትር ሼን ቺንሚን ገለጹ፡፡
ሚኒስትር አማካሪው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ፥ የሀገራቱ ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራትን ኢኮኖሚ ያስችላል በሚል ይፋ ያደረጓቸው ዘጠኝ ፕሮጀክቶች ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር የምታደርገው ትብብር ፍኖተ ካርታ መሆኑንም አስረድተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቅርብ ጊዜ ከቻይናው አቻቸው ቺን ጋንግ ጋር በሀገራቱ መካከል እያደገ የመጣውን ዘርፈ ብዙ ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን አስታውሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ የቻይና ባለሃብቶችን ለመሳብ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው ፥ ጥረቱን ፍሬያማ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
አማካሪ ሚኒስትሩ አያይዘውም በአዲስ አበባ ከተማ በቻይናውያን የተገነቡ በርካታ ፕሮጄክቶች መኖራቸውን በመጥቀስ፥ ይህም የሁለቱ ሀገራት የማህበረ – ኢኮኖሚ ግንኙነት ምን ያክል ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዳደገ ማሳያ መሆኑን አውስተዋል።
ቻይና ምንጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያን የማደግና የመበልጸግ ፍላጎት እንደምትደግፍም የገለጹት አማካሪ ሚኒስትሩ፥ ሀገራቸው የአንድ ወገን ሳይሆን የትብብር ፕሮጀክት ትፈልጋለች ብለዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ መንግስትና ከኢኮኖሚ ዘርፍ ተዋናዮች ጋር በትብብር በመስራት ኢትዮጵያ ያስፈልጓታል ባልናቸው ዘርፎች ላይ ተሳትፎ እናደርጋለንም ነው ያሉት፡፡
ከአህጉሪቱ ጋር ለውን ግንኙነት ሲያነሱም የአፍሪካ ወጣቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላቸውን ፍላጎት በማገዝ ዙሪያ ትኩረት እንደሚደረግም ነው ያነሱት፡፡
በቻይና አፍሪካ ትብብር መድረክ እና በቻይና ስፔስ ኢንጂነሪንግ ፅህፈት ቤት የቻይና ክትትል ኮሚቴ ሴክሬታሪያት ማይ ድሪም ወይም “ህልሜ” በሚል መሪ ቃል የስዕል ውድድር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ውድድሩ የአፍሪካ ተማሪዎችን ለማነሳሳት ያለመ እንደሆነም ነው የጠቀሱት፡፡
ውድድሩ በዋናነት በአዲሱ ትውልድ ተሰጥዖ ላይ ፈሰስ በማድረግ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ እድገትና ብልጽግናን የመደገፍ ትልም እንዳለው አንስተዋል።
በስፔስ ሳይንስ ላይ ያተኮረው የሥዕል ውድድር አፍሪካውያን ተማሪዎች ህልማቸውን እንዲያዩ እና አቅማቸውን እንዲያሳድጉ እድል እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።
በወንድወሰን አረጋኸኝ
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!