የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአውሮፓ ህብረት ፕሮጀክቶችን አሸነፈ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ህብረት ከሚደግፋቸው 17 የምርምር እና የትምህርት ልህቀት ማዕከላት ፕሮጀክቶች አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዘጠኙ አሸናፊ መሆኑ ተገለፀ።
በተጨማሪም ሁለት የፕሮጀክት ፕሮፖዛሎች ውጤት በመዎቹው ጥቂት ወራት ይታወቃሉ ተብሏል።
በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን በ2022 ኅዳር ወር ላይ የአፍሪካ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ጥምረት (ARUA) እና የአውሮፓ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ጥምረት (Guild) የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች በነበራቸው ስብሰባ በአውሮፓ ህብረት የሚደገፉ የምርምር እና የ ትምህርት ልህቀት ማዕከላት ለማቋቋም ወስነው መለያየታቸው ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በርካታ ፕሮፖዛሎች የቀረቡ ሲሆን÷ ባለፉት ሁለት ተከታታይ ቀናት በቤልጂየም ብራስልስ በተካሄደው ግምገማ 17 የልህቀት ማእከል መመስረታቸውን ከዩኒቨርሲቲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከእነዚህ የልህቀት ማዕከል ፕሮጀክቶች ውስጥም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዘጠኙ አሸናፊ ሆኗል ነው የተባለው።
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ፕሮጀክቶቹን በማሸነፉ በሚሊየኖች የሚቆጠር ዩሮ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጣሰው ወልደሃና (ፕ/ር) በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ፥ ይህ ውጤት ለዩኒቨርሲቲውም ሆነ ለሀገር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰው ለዚህ ውጤት አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል፡፡