Fana: At a Speed of Life!

የሸኔ አባል በመሆን በፀጥታ አካላት ላይ ጦርነት ከፍተዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሸኔ የሽብር ቡድን አባል በመሆን በመንግስት የፀጥታ አካላት ላይ ጦርነት በመክፈት ሲዋጉና ለቡድኑ የገንዘብ ድጋፍ ሲያሰባስቡ ነበር በተባሉ በሦሥት ግለሰቦች ላይ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ።

የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ለፖሊስ የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የፀረ-ሽብር ወንጀል መርማሪ በተጠርጣሪዎቹ ህገ-መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ በማቀድ የሸኔ ሽብር ቡድን አባል በመሆን፣ የመንግስት የፀጥታ አካላት ላይ ጦርነት በመክፈት፣ የሎጀስቲክ ድጋፍ በማሰባሰብ ሲንቀሳቀሱ ነበር በማለት ፖሊስ የጥርጣሬ መነሻወችን ጠቅሶ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አቅርቧል።

በዚህ መነሻ የተጠርጣሪዎች የጣት አሻራ ማስነሳቱን፣ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ሥርዓት ህግ ቁጥር 27/2 መሰረት የተጠርጣሪዎችን ቃል መቀበሉን፣ የፎረንሲክ ምርመራ ውጤት ከሚመለከተው አካል እንዲሰጠው መጠየቁን እና የገንዘብ ዝውውርን ለማጣራት ከተለያዩ ባንኮች ማስረጃ እንዲሰጠው በደብዳቤ መጠየቁን መርማሪው ጠቅሷል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ÷ የተጠርጣሪዎቹ የተሳትፎ ደረጃ ባልተገለጸበት ሁኔታ ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቁ አግባብ አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል።

በተጨማሪም ÷ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ ከመንግስት የሚሰበሰብ ማስረጃን የማጥፋት አቅም እንደሌላቸው ጠቅሰው ፤ የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ÷ አንደኛ ተጠርጣሪ በዓለም ገና ከሌሎች ግብረአበሮቹ ጋር በመሆን በፀጥታ አካላት ላይ ጦርነት ከፍቶ ከተመታ በኋላ ለህክምና አዲስ አበባ በመጣበት ወቅት በቁጥጥር ስር መዋሉን አብራርቷል።

3ኛ ተጠርጣሪን በሚመለከት ከዚህ በፊት ታስራ እንደነበር ጠቅሶ ፥ በድጋሚ ሳትታረም ከሸኔ የሽብር ቡድን አመራሮች ጋር በመገናኘት ወደ ሽብር ቡድኑ በመቀላቀል ለቡድኑ ገንዘብ ማሰባሰብ ስራ ላይ ተሰማርታ ስትንቀሳቀስ በቁጥጥር ስር መዋሏን አስረድቷል።

ተጠርጣሪዎቹ ቢወጡ ምስክር ሊያስፈራሩና ወደ ሽብር ቡድኑ ተቀላቅለው በድጋሚ ተመሳሳይ ተግባር ሊፈጽሙና ላይገኙ ይችላሉ በማለት ስጋቱን ገልጾ ፥ የዋስትና ጥያቄያቸውን ተቃውሟል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ተጠርጣሪዎቹ ቢወጡ ወደ ሽብር ቡድኑ ሊቀላቀሉ ይችላሉ የሚለውን የፖሊስ ስጋት ምክንያታዊ ነው በማለት ድምዳሜ ላይ መድረሱን ጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን የተመለከቱት ዳኛ አብራርተዋል።

ከቀሪ ስራዎች አንጻር ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊነትን በማመን የተጠርጣሪዎች የዋስትና ጥያቄን ውድቅ በማድረግ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ ተፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.