Fana: At a Speed of Life!

የተጀመረው የፍትህ ተቋማት የለውጥ ፍኖታ ካርታ ትግበራ በትኩረት ሊሰራ ይገባል-አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፍትህ ለሰላም፣ ለዘላቂ ልማትና ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዋሳኝ ሚና ስላለው የተጀመረው የፍትህ ተቋማት የለውጥ ፍኖታ ካርታ ትግበራ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

3ኛው ሀገር አቀፍ የህግ አውጪዎች የጋራ የምክክር መድረክ በጅግጅጋ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

አፈ-ጉባኤ ታገሰ÷ መድረኩ በመንግስታት መካከል ያለውን ግንኙነት ለመወሰን የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1231/2013 መሰረት በማድረግ በፌዴራል እና በክልሎች መካከል ያለ ግንኙነትን ለማጠናከር በየስድስት ወሩ የሚካሄድ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

ፍትህ ለማረጋገጥና ለማጠናከር በፌዴራል የፍትህ ተቋማት የተጀመረው የፍትህ የለውጥ ፍኖታ ካርታ በየደረጃው ያሉ የፍትህ ተቋማት ለመተግበር መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።

“ፍትህ ለሰላም፣ ለዘላቂ ልማት፣ ለፖለቲካና ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ ሚና አለው” ሲሉም አፈ-ጉባኤው ተናግረዋል።

በህግ አውጪዎች መካከል የሚደረገው ውይይት ዘላቂ ሰላምን በማስፈን፣ ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ ለማረጋገጥ እና ፈጣን እድገት በማስመዝገብ፣ አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያግዛልም ብለዋል።

የክልሎች እና የብሄረሰቦች ምክር ቤቶች እየተሳተፉበት በሚገኘው የምክክር መድረክም የእርስ በእርስ ግንኙነትን ከማጠናከር ባሻገር መልካም ተሞክሮዎች የሚለዋወጡበት እንደሆነም ጠቁመዋል።

መድረኩ በፌዴራል ደረጃ በፍትህ ስርዓቱ ላይ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን በክልሎችም ለማጠናከር የሚያግዝ ምክክር ይካሄድበታል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ÷እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት በየደረጃው የሚገኙ የፍትህ ተቋማት ተቋማዊ ነፃነታቸው ተጠብቆ በሰው ኃይል እና በቴክኖሎጂ ታግዘው መስራት ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.