ጫናን መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ ለመገንባት የታክስና ጉምሩክ ሕግ ተገዢነትን ማስፈን እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠንካራና ጫናን መቋቋም የሚችል ሀገራዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት የታክስና ጉምሩክ ሕግ ተገዢነትን ማረጋገጥ ከሁሉም ባለድርሻዎች የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር ገለጸ።
የደቡብ ክልል ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች የዕውቅናና ሽልማት መርሐ ግብር የክልልና የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ቱሉ÷ የግብር ሥርዐቱን በማክበርና በማስከበር ጠንካራና ጫናን መቋቋም የሚችል ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ ኢኮኖሚ መገንባት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በመሆኑም ጠንካራ የታክስ ሥርዐትን መገንባትና የታክስና ጉምሩክ ሕግ ተገዢነትን ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻዎች በትኩረት መስራት እንደዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በሀገር ደረጃ ይህንን ለማሳካት የሚያስችል የታክስና ጉምሩክ ሕግ ተገዢነት ንቅናቄ “ግብር ለሀገር ክብር” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ እንደሚገኝ አስታውሰዋል።
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ÷ ከውጭ እርዳታና የኢኮኖሚ ጫና ተላቀን ሀገራችንን በራሳችን አቅም ማሳደግና ማልማት የምንችለው የውስጥ ገቢያችን ላይ በትኩረት መሥራት ስንችል ነው ብለዋል።
ለዚህም የተፈጥሮና የሰው ሃይል ፀጋዎችን ተጠቅሞ ኢኮኖሚን ማሳደግና ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ተገቢውን ግብር በአግባቡ መሰብሰብ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በታማኝነት መክፈላቸውን አጠናክረው በማስቀጠል በሀገራቸው ልማትና እድገት የበኩላቸውን አሻራ እንዲያኖሩ ጥሪ አቅርበዋል።