በጃክ ማ ለአፍሪካ ሀገራት የተበረከቱ 3ኛ ዙር የኮሮና ቫይረስ የህክምና ቁሳቁሶች ዛሬ አዲስ አበባ ደረሱ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 19፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሊባባ ፋውንዴሽን መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ጃክ ማ ለአፍሪካ ሀገራት የተበረከቱ ሶስተኛ ዙር የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶች ዛሬ አዲስ አበባ ደርሰዋል።
በዚህም ለአፍሪካ ሀገራት የተላኩ 4 ነጥብ 6 ሚሊየን ማስኮች፣ 500 ሺህ ናሙና መውሰጃ እና መመርመሪያዎች፣ 300 የመተንፈሻ መሳሪያዎች፣ 200 ሺህ አልባሳትና 200 ሺህ የፊት መሸፈኛዎች ነው አዲስ አበባ የደረሰው።
በተጨማሪም ከድጋፍ ውስጥ 2 ሺህ የሙቀት መለኪያዎች፣ 100 የሰውነት መለኪያ መሳሪያዎች እንዲሁም 500 ሺህ ጥንድ የእጅ ጓንቶችም ይገኙበታል።
በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ እና ሎጅስቲክ አገልግሎት በተደረገው የርክክብ ስነ ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ መንግስት እና የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
ጃክ ማ በመጀመሪያው ዙር ለእያንዳንዱ የአፍሪካ ሃገር ቫይረሱን ለመለየት የሚረዱ 20 ሺህ መመርመሪያዎች፣ 100 ሺህ የፊት ጭምብል፣ የህክምና ባለሙያዎች የሚለብሷቸው 1 ሺህ መከላከያ ልብሶች ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በተመሳሳይ በሁለተኛው ዙር ድጋፍም 500 የመተንፈሻ መሳሪያዎች (ቬንትሌተር)፣ 200 ሺህ የፊት መሸፈኛዎችና የህክምና ሙሉ ልብሶች፣1 ሚሊየን ናሙና መውሰጃ ፣ 2 ሺህ የሰውነት ሙቀት መለኪያ እና 500 ሺህ ጓንቶች ለአፍሪካ ሀገራት ልከዋል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።