ስፓርት

ለሀምበርቾ እግር ኳስ ቡድን 2 አውቶብሶች እና የ250 ሺህ ብር ሽልማት ተበረከተ

By Melaku Gedif

June 10, 2023

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ከልል መንግስት ክልሉን ወክሎ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለተቀላቀለው የሀምበርቾ እግር ኳስ ቡድን የተለያዩ ማበረታቻዎችንና የእውቅና ሰርተፊኬት አበርክቷል።

በመርሐ ግብሩ የተገኙት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ ስፖርት ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ርስቱ ይርዳ የክልሉን ስፖርት ለማሳደግ መንግስት አበክሮ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ክልሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደማቅ ታሪክ የሰሩ ስፖርተኞች መፍለቂያ መሆኑንም ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ የሀምበርቾ እግር ኳስ ክለብ አባላት የክልሉ አምባሳደር እንደሆኑም አስገንዝበዋል።

ስፖርቱ ሕዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ሰፊ መሰረት መጣሉን ገልጸው÷ የአርሶ አደሩና የአርብቶ አደሩ ተሳታፊነት እንዲያድግ እየተሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

የክልሉ መንግስትና ሕዝብም ለሀምበርቾ እግር ኳስ ወንዶችና ሴቶች ክለብ ሁለት አውቶብሶች እና 250 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል ነው ያሉት፡፡

የሀምበርቾ እግር ኳስ ቡድን በሴቶችም በወንዶችም እግር ኳስ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በመቀላቀሉ መደሰታቸውን እና ድጋፉም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።