የሐረሪ ቋንቋን ከማሳዳግ ረገድ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ – አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ቋንቋን ከማሳዳግ ረገድ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት የሐረር መምህራንና ትምህርት ቢዝነስ ኮሌጅ በሐረሪ ቋንቋና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ለመጀመሪያ ጊዜ በዲግሪ መርሐ ግብር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎቹን ባስመረቀበት ወቅት ነው ።
ኮሌጁ ለተከታታይ አራት ዓመታት በሐረሪ ቋንቋና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ በኤክስቴንሽን መርሐ ግብር ያሰለጠናቸውን 62 ተማሪዎቹን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
በምርቃት ስነ ስርዓቱ ወቅት የተገኙት የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንደገለፁት ፥ የሐረሪ ቋንቋ እየሰፋ፣ እያደገና ከትውልድ ወደ እየተሸጋገረ ያለ ቋንቋ ነው።
ቋንቋው እንዲያድግ ኮሌጆችና ሌሎች ተቋማት እያከናወኑት ያሉት ተግባራት የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል ።
በቀጣይም የሐረሪን ቋንቋ የማስፋፋትና ተደራሽ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የሐረሪ ቋንቋን ተጠብቆ ከትውል ወደ ትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ተመራቂ ተማሪዎች ሀገራዊ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡም ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል ።
የሐረር መምህራን እና ቢዝነስ ኮሌጅ ዲን አቶ ጃሚእ መሐመድ በበኩላቸው ፥ ኮሌጁ ለ70 ዓመታት በተለያዩ ሙያ ዘርፎች ዜጎችን ሲያሰለጥን ቆይቷል።
ለመጀመሪያ ጊዜም በዲግሪ መርሐግብር በሐረሪ ቋንቋና እና በኮሙኒኬሽን ትምህርት ዘርፍ አስመርቋል ብለዋል።
ተማሪዎችም በሰለጠኑበት ሙያ መስክ ማህበረሰቡን በቅንነትና በታማኝነት እንዲያገለግሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዕለቱም በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የማበረታቻ ሰርተፍኬት ሽልማት መበርከቱን ከክልሉ መንገስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡