ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከሩሲያ አምባሳደር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ከሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)÷ የኢትዮጵያና ሩሲያ ግንኙነት ዘመናትን ያስቆጠረ ነው ብለዋል።
የረጅም ዘመን ግንኙነታቸውን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በተለያዩ የትብብር ዘርፎች በጋራ እንደሚሰሩም መግለጻቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል።
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን በበኩላቸው÷ሀገራቸው ሩሲያ በትምህርት፣ በኢንቨስትመንትና በተለያዩ የልማት ዘርፎች በጋራ የመስራት ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
በውይይቱ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ጌታቸው ጀምበር (ዶ/ር)፣ በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳድር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) እንዲሁም በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮነን ተገኝተዋል።