የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ መድረክ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መልሶ ማቋቋምና ግንባታ መድረክ ተካሂዷል፡፡
መድረኩ በሁለት ዓመቱ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የደረሱ ውድመቶችን መልሶ መገንባት ላይ እንደሚያተኩር ተገልጿል፡፡
በመድረኩ ሚኒስትሮች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።
እየተካሄደ ባለው ፓናል ውይይትም ከሠላም ሥምምነቱ በኋላ የጤና፣ የቴሌኮምና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ ሥራ ማስጀመር መቻሉ ተነስቷል፡፡
የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ÷ በአማራ ክልል ፣ በትግራይና አፋር ክልሎች ጦርነቱ በጤናው ዘርፍ ጉዳት ማድረሱን ገልጸው ከሥምምነቱ በኋላ አገልግሎቶችን ለማስጀመር መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሰርቷል ብለዋል።
በዚህም ውድመት የደረሰባቸውን ጤና ተቋማት ዳግም ሥራ ለማስጀመር ጉዳት የደረሰባቸውን ሆስፒታሎች በአዲስ አበባ ከሚገኙ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የፀጥታ ችግር ለጤና አገልግሎቱ እንቅፋት መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢፌዴሪ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው ÷ በግጭት ቀዳሚ ተጎጂዎቹ ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ግጭቶች እንዳይከሰቱና ጉዳታቸውን ለመቀነስም ሴቶች የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ጦርነቱ ያለያያቸውን ቤተሰቦች ዳግም ማገናኘት እንዲሁም የሥነ-ልቦናና ማኅበራዊ ድጋፎችን ማድረግ በመልሶ ማቋቋም ሥራው ትኩረት ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ÷ የሰሜን ኢትዮጵያን ችግር ጨምሮ በኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉልና ሌሎች አካባቢዎች ይንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎችን ወደ ሠላማዊ ሕይወት ለመመለስና መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ ነው ብለዋል።
ሆኖም ሂደቱ ከፍተኛ ገንዘብ እና የአጋር አካላትን ርብርብ እንደሚፈልግም ነው የተናገሩት።
የተቋሙን አቅም ለማሳደግ መሥራት ይጠይቃልም ብለዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምሕረቱ ÷ በድኅረ-ግጭት ወቅት በምጣኔ ሐብት ላይ የሚከሰተውን ጫና ለመመከት የውጭ ምንዛሬ ክምችት ለማሳደግ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
የዋጋ ግሽበቱንም ለማረጋጋት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ÷ በየክልሎቹ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ እንቅስቃሴዎች መሻሻል አሳይተዋል ብለዋል።
ተፈናቃዮችን መልሶ ማቋቋምና መሰረተ ልማቶችን መገንባት እንደሚያስፈልግም ነው በአጽንኦት የገለጹት፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው÷ በምዕራብና ደቡብ የክልሉ አካባቢዎች በግጭቶች ውድመት መድረሱንና በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት ጥረቶች መቀጠላቸውን ተናግረዋል፡፡
ታጣቂዎች የሚያደርሱት ጥቃት ከማህበራዊ ተቋማት ውድመት ባለፈ በግብርና ስራ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ነው የጠቆሙት፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን÷ በክልሉ ያሉ ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ትኩረት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡
በአፈወርቅ እያዩ