የልብ ጤንነትን የሚጎዱ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ የጤና ሁኔታዎች እና የአኗኗር ዘይቤዎች የልብ ህመም ተጋላጭነትን ሊጨምሩ ይችላሉ።
ዋና ዋናዎቹም
ከፍተኛ የደም ግፊት
ከፍተኛ የደም ግፊት ለልብ ህመም የሚያጋልጥ ሲሆን÷ ቁጥጥር ካልተደረገበት ኩላሊትን እና አንጎልን ጨምሮ ልብን እንዲሁም ሌሎች ዋና ዋና የሰውነት ክፍሎችን ሊጎዳ ይችላል።
የኮሌስትሮል መጠን መጨመር
ሰውነት ሊጠቀምበት ከሚችለው በላይ ኮሌስትሮል ካለ በደም ቧንቧዎች ግድግዳ ላይ ሊከማች እንደሚችል እና ይህም የሰውነትን የደም ዝውውር እንደሚቀንስ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የስኳር በሽታ
የስኳር በሽታ በደም ውስጥ ስኳር እንዲከማች ያደርጋል።
የስኳር በሽታ ላለባቸው ሰዎች በልብ በሽታ የመሞት ዕድላቸው የስኳር በሽታ ከሌለባቸው ሰዎች የበለጠ መሆኑም ይነገራል፡፡
ሲጋራ ማጨስ እና ለሲጋራ ጭስ መጋለጥ
ሲጋራ ማጨስ ልብን እና የደም ሥሮችን ይጎዳል፡፡
ይህም እንደ ኤቲሮስክሌሮሲስ እና የልብ ድካም ላሉ የልብ ህመም የመጋለጥ እድልን ይጨምራል።
ከመጠን በላይ ውፍረት እና ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ
ከመጠን በላይ መወፈር የሰውነት ስብ እንዲከማች ስለሚያደርግ “መጥፎ” ኮሌስትሮል እና ትራይግሊሰርራይድ ደረጃዎች እንዲጨምሩ በማድረግ “ጥሩ” የኮሌስትሮል መጠንን ይቀንሳል።
ከመጠን በላይ መወፈር ለደም ግፊት እና ለስኳር ህመም እንዲሁም ለልብ ህመም ይዳርጋል።
በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ
በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ለልብ ህመም ያጋልጣል፡፡
በተጨማሪም ለውፍረት፣ ለደም ግፊት፣ ለከፍተኛ ኮሌስትሮል እና የስኳር በሽታ ተጋላጭነት ይጨምራል።
አልኮል መጠጣት
ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት የደም ግፊትን ከፍ ሊያደርግና ለልብ በሽታ ሊዳርግ ይችላል።
ጤናማ ህይወት ለመምራትና ከልብ በሽታ ራስዎን ለመጠበቅ ከላይ ከተጠቀሱት አጋላጭ ሁኔታዎች ራስዎን ይጠብቁ።