Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ 116 ሰዎች ተሰብስበው ሺሻ ሲያጨሱ በቁጥጥር ስር ውለዋል

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 19 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 በተለምዶ ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ ከህዝብ የደረሰውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ ፖሊስ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ 116 ሰዎች ተሰብስበው ሺሻ ሲያጨሱ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የኮሮና ቫይረስ (የኮቪድ 19) ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ብሎም ጉዳቱን ለመቀነስ በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተከለከሉ ተግባራት መካከል በማንኛውም ቦታ የሺሻ ማስጨስና ጫት ማስቃም አገልግሎት መስጠት መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ክልከላዎቹ ሲጣሱ ይስተውላል።

ሰዎቹ ሚያዚያ 18 እና 19 ቀን 2012 ዓ.ም በተለያዩ ሰዓታት በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ራሄል ሆቴል ውስጥ 35 ሰዎች እንዲሁም ቲሊሊ በሚባል ሆቴል ውስጥ 81 ግለሰቦች ተሰብስበው ሺሻ ሲያጨሱ ከህዝብ በደረሰው ጥቆማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዲቪዚዮን ሃላፊ ኮማንደር ጃፋር ኸሊል ገልፀዋል።

በተመሳሳይ በዚህ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ስምንት ሰዎችን በአንድ አነስተኛ ጠባብ ቤት ውስጥ ጫት ሲያስቅም የተገኘ ግለሰብም በቁጥጥር ስር መዋሉን የክፍለ ከተማው አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ሃላፊ ወይዘሮ ሠጂዳ ሙሰማ ተናግረዋል።

ኮማንደር ጃፋር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ድንጋጌን በሚጥሱ ግለሰቦች ላይ የሚወሰደውን እርምጃ በተመለከተ በህጉ አግባብ አስፈላጊ መረጃዎች መሰብሰባቸውን ገልፀው የምርመራ መዝገቡን አደራጅቶ በሚመለከተው የፍትህ አካል ክስ እንደተመሰረተባቸው አስረድተዋል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገጉ የመብት እገዳዎችን፣ እርምጃዎችን፣ የተሰጠ መመሪያን፣ ትዕዛዝን የጣሰ ማንኛውም ሰው እስከ 3 አመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከ 1 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ ቅጣት እንደሚቀጣ መደንገጉን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.