Fana: At a Speed of Life!

በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ያለ አግባብ የእስር እና አስገድዶ መድፈር ወንጀል እንዲፈጸም አድርገዋል የተባሉ 5 ተከሳሾች ከአንዱ በቀር ሌሎቹ ነፃ ተባሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአርቲስት አረጋኸኝ ወራሽ በተሰጣት ውክልና ከውጭ የገባ የሙዚቃ መሳሪያ እንድትመልስ በማስፈራራት የግል ተበዳይ እንድትታሰርና የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንዲፈጸምባት አድርገዋል ተብለው የተከሰሱ ግለሰቦች ነጻ ተባሉ።
በዚሁ መዝገብ ላይ የግል ተበዳይ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በታሰረችበት ወቅት የዕለቱ ተረኛ ጥበቃ ወታደር የነበረው 5ኛ ተከሳሽ የመድፈር ወንጀል መፈፀሙ በማስረጃ በመረጋገጡ በቀረበበት ክስ የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቶበታል።
የጥፋተኝነት ፍርዱን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
በቀረበባቸው የወንጀል ክስ ላይ በዛሬው ቀጠሮ ሙሉ በሙሉ ነጻ የተባሉት ተከሳሾች 1ኛ- ተከሳሽ በአዲስ አበባ ፖሊስ የአየር መንገድ ፖሊስ ጣቢያ የወንጀል ምርመራ ሀላፊ ምክትል ኢንስፔክተር መንግስቱ ገብረሚካኤል፣ 2ኛ- ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፖሊስ ጣቢያ መርማሪ ዋና ሳጅን ቦሴ ለምለሙ ሙልዬ፣ 3ኛ- የቀድሞ የመከላከያ አባል ሻለቃ ዮሐንስ አበበ ፣ 4ኛ- በግል ስራ ላይ ይተዳደራል የተባለው አደም ሰይድ መሀመድ ናቸው።
የዐቃቤ ህግ ክስ በተከሳሾቹ ላይ አቅርቦት በነበረው ክስ የግል ተበዳይ የሙዚቃ መሳሪያዎች ከውጪ ለማስገባትና ጉዳይ ለማስፈጸም ከአርቲስት አረጋኸኝ ወራሽ ሚያዚያ 6 ቀን 2014 ዓ.ም ውክልና መሰረት እቃዎችን ከውጭ ማስገባቷን አመላክቷል።
ነገር ግን 4ኛ ተከሳሽ የአርቲስት አረጋኸኝ ወራሽ ውክልና ስላለኝ ንብረቱን መልሺልኝ በማለት በጠየቀበት ጊዜ የግል ተበዳይም እቃውን ከውጭ ለማስገባት ለቀረጥና ለጉምሩክ ሰራተኞች የከፈለችውን አጠቃላይ 3 ሚሊዮን 200 ሺህ ብር በቅድሚያ እንዲከፍላት ትጠይቃለች፡፡
ይህን ተከትሎም 4ኛ ተከሳሽ ጉዳዩን በሕጋዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ከ1ኛ፣ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ጋር በመመሳጠር ወደ መኖሪያ ቤቷ በመሄድ ንብረቱን እንድትመልስ በማስፈራራት፣ በመዛት፣ ያለአግባብ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፖሊስ ጣቢያ እንድትታሰር እና በዕለቱ ጥበቃ እንድትደፈር አድርገዋል በሚል ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል።
ተከሳሶቹ በአጠቃላይ በዐቃቤ ህግ የቀረበባቸው 3 ክስ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አልፈፀምንም በማለት የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ህግ አርቲስት አረጋኸኝ ወራሽን እና የግል ተበዳይን ጨምሮ አጠቃላይ ስምንት ምስክሮች እና የለተያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱ የምስክር ቃልና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ ዛሬ በዋለው ችሎት ከ1 እስከ 4ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች በክሱ ላይ የተጠቀሰባቸውን የወንጀል ድርጊት አጠቃላይ ስለመፈጸማቸው በሰውም ሆነ በሰነድ ማስረጃ አለመረጋገጡ ተገልጿል።
በተለይም 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የሙዚቃ መሳሪያው እንዲመለስለት 4ኛ ተከሳሽ ባቀረበው አቤቱታ መሰረት በህግ የተሰጣቸው ኃላፊነትን በመጠቀም በመኖሪያ ቤት ብርበራ እና ምርመራ እንዲደረግ ከማድረግ ባሻገር ስልጣናቸውን ተጠቅመው ሰብአዊነት የጎደለው ተግባር አለመፈጸማቸው ተጠቅሷል።
በተጨማሪም የግል ተበዳይ የአስገድዶ መድፈር ተፈጸመብኝ ብላ በተናገረችበት ወቅት በራሳቸው ተነሳሽነት ወደ ህክምና ተቋም እንደወሰዷት በጉዳዩም ማዘናቸውን በግል ተበዳይ በምስክርነት ቃል መሰጠቱንም ችሎቱ አረጋግጧል።
በዚህም መሰረት ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ሁሉም ተከሳሾች በነጻ እንዲሰናበቱ በሙሉ ድምጽ ተወስኗል።
በዚሁ መዝገብ ላይ በ5ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሰው 5ኛ ተከሳሽን በሚመለከት የግል ተበዳይን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ያለአግባብ በታሰረችበት ወቅት የዕለቱ ተረኛ ጥበቃ በግሉ ሀሳብና ተነሳሽነት አስገድዶ ስለመድፈሩ በማስረጃ በመረጋገጡ በሌለበት የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቶበታል።
በተከሳሹ ላይ በዐቃቢ ህግ የሚቀርበውን የቅጣት አስተያየት ለመመልከት ለሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.