“ዲጂታል ኢትዮጵያ”ን ዕውን ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “ዲጂታል ኢትዮጵያ”ን ዕውን ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።
7ኛው የአፍሪካ ኢኖቬሽንና ዲጂታል ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ኢትዮጵያ ለ”ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ” ዘርፍ ትልቅ ትኩረት መስጠቷን ሚኒስትሩ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተለይም በ”ቴሌኮም ሴክተሩ” ሠፊ የለውጥ ሥራ መሠራቱ የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ቁጥር በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ማስቻሉን ነው የተናገሩት።
አክለውም ኢኮኖሚውን ለመደገፍ የተጀመረው የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት እመርታ እያስመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሥርዓቱ ለሥራ ፈጠራ ፣ ኢንቨስትመንት፣ የመረጃ እና ለቴክኖሎጂ ተደራሽነት እንዲሁም ለተለያዩ አገልግሎቶች መዘመን ትልቅ አበርክቶ እንዳለውም አስረድተዋል።
በቀጣይም የዲጂታል ሥርዓቱን ይበልጥ ለማጠናከር እና ሌሎች ዘርፎችንም በመስኩ ለማሥፋት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘርፉ ከተለያዩ አካላት ጋር የሚደረጉ ውሎች እና ሥምምነቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል፡፡
የዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ኅብረት ተወካይ ካሮሊን ጋውዡ በበኩላቸው÷ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ሀገራት የዲጂታል አገልግሎት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና ቁጥጥር ዋና ኃላፊ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ በበኩላቸው ÷ “ሳፋሪኮም” ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ እየሠራ መሆኑን አንስተዋል።