Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካ እና እስያ ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲያስመዘግቡ የአህጉራቱ ወጣቶች ትብብራቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል – ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 7 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካ እና እስያ ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲያስመዘግቡ የአህጉራቱ ወጣቶች ትብብራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) አመለከቱ።

በኦ የስ ግሎባል ፋውንዴሽን አዘጋጅነት ላለፉት ሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ እና እስያ ወጣቶች ፎረም ዛሬ ተጠናቋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፥ አፍሪካና እስያ በልማት ዙሪያ የሚገጥማቸውን ችግሮች ለመሻገር ወጣቶችን ማሳተፍ የግድ ይላቸዋል።

“እናንተ የአህጉራቱ ወጣቶች የነገ ብቻም ሳይሆን የዛሬ መሪዎች ናችሁ፤ “አህጉራቱ ውጤታማ የልማት ጉዞ እንዲያራምዱ የድርሻችሁን ልትወጡ ይገባል” ብለዋል።

ወጣቶች ትልቅ አቅም በመሆናቸው የአህጉራቱ መሪዎች ወጣቶችን የሚያበቁ ተግባራትን በተጠናከረ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባቸዋልም ነው ያሉት።

የኦ የስ ግሎባል ፋውንዴሽን የክብር አምባሳደር አክ ቦርሀሙዲን በበኩላቸው፥ በርካታ ሀገራት በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2030 ዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ግብ እንደያዙ አንስተዋል።

ግቦቹ የሚሳኩት ወጣቶች በስራ ዕድል ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ፣ ጤና እና ሌሎች መስኮች ምቹ ሁኔታ ሲፈጠርላቸው መሆኑን ገልጸው በዚህ ላይ ሀገራት የበለጠ ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በመሆኑም የእስያ እና አፍሪካ ወጣቶች በጋራ የሚመክሩበትና ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት መድረክ መፈጠሩ ለዘላቂ ልማት ግቦች መሳካት ትልቅ ግብዓት ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በፎረሙ ከሁለቱ አህጉራት የተውጣጡ ወጣቶች እና ተወካዮች ተሳትፈዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.