Fana: At a Speed of Life!

ለከፍተኛ የደም ግፊት የሚጋለጡት የትኞቹ ሰዎች ናቸው?

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ከጠቅላላው ህዝብ 20 ከመቶ የሚሆኑት ሰዎች ከፍተኛ የደም ግፊት መጠን እንዳላቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ከፍተኛ የደም ግፊት እንዳለባቸው አያውቁም ነው የተባለው፡፡

ከፍተኛ የደም ግፊት መኖር ለአጣዳፊ የልብ ውጋት ወይም በደም ዝውውር ማነስ ምክንያት ለሚከሰት የአዕምሮ ስራ መታወክና ለጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ የመጋለጥ ዕድልን እንደሚጨምርም የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ለመሆኑ ለከፍተኛ የደም ግፊት ተጋላጭ የሚሆኑት ምን አይነት ሰዎች ናቸው?

ለከፍተኛ የደም ግፊት ተጋላጭ የሚሆኑ ሰዎች ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በላይ የሆኑ፣ በተለይም ከ45 ዓመት በላይ የሆኑ፣ የሰውነት ክብደታቸው ከፍተኛ የሆነ፣ የኩላሊት በሽታ ያለባቸው፣ የስኳር በሽታ ያለባቸው፣ የደም ግፊት በሽታ በቤተሰባቸው ታሪክ ያለባቸው፣ ወይም በበሽታው የተጠቃ የቅርብ ዘመድ ካለ እንዲሁም ብዙ ጊዜ የሚጨናነቁ ሰዎች ናቸው፡፡

እንዲሁም የሰውነት እንቅስቃሴ የማያዘወትሩ፣ ሲጋራ የሚያጨሱ ወይም አደንዛዥ እጽ የሚጠቀሙ፣ የአልኮል መጠጥ የሚያዘወትሩ፣ ብዙ ጊዜ ጨው የበዛበት ምግብ የሚመገቡ፣ በቂ ፍራፍሬና አትክልት የማይመገቡ ናቸው፡፡

ከፍተኛ የደም ግፊት ሲኖር የህመም ስሜት ወይም ሌሎች ምልክቶች ላይታዩ ወይም ላይኖሩ እንደሚችሉ ከጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ስለዚህ የእርስዎም የደም ግፊት መጠን ከፍተኛ ከሆነ እና በጊዜው ህክምና ካላደረጉ ለከፍተኛ የልብ በሽታና በደም ዝውውር ማነስ ምክንያት ለሚከሰት የአዕምሮ ስራ መታወክ የመጋለጥ ዕድልዎ እጅግ በጣም ከፍተኛ ይሆናል፡፡

በዚህም የደም ግፊትዎን መጠን ማወቅ ሕይወትወን ሊያድን ይችላልና የደም ግፊትዎን በየጊዜው ቢለኩ መልካም ነው፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.