Fana: At a Speed of Life!

የሱዳን ችግር በሚፈታበት አካሄድ የኢጋድ አባል ሀገራት አንድ አይነት አቋም ላይ መድረሳቸው ተመለከተ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 8 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጅቡቲ በተካሄደው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) አባል ሀገራት ጉባኤ አባል ሀገራቱ የሱዳን ችግር በሚፈታበት አካሄድ ላይ አንድ አይነት አቋም ላይ መድረሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የሚኒስቴሩን ሳምንታዊ መግለጫ የሰጡት ቃል አቀባዩ አምባሳደር መለስ አለም ÷ስብሰባው በዋናነት የሱዳንን ጉዳይ በትኩረት ተመልክቶ የቀጣይ መፍትሄ አምጭ ውሳኔዎችን ማስቀመጡን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ አራት የቀጠናው ሀገራት ችግሩን ለመፍታት አስቻይ ስራዎችን እውን እንዲያደርጉም ተመርጠዋል ነው ያሉት።

አራቱ ሀገራት ከ10 ቀናት በኋላ በአዲስ አበባ ተገኝተው እንደሚመክሩና ውሳኔዎችን እንደሚያስቀምጡ ተጠቁሟል።

በዚህም÷ ኢትዮጵያ በሱዳን ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን የቀደመ ፍላጎቷን አጠናክራ መቀጠሏ ጉልህ ማሳያ መሆኑ ተመላክቷል።
የኤርትራ ከረጅም ዓመታት በኋላ ወደ ኢጋድ መመለሷ ሌላው የጉባኤው ስኬት መሆኑን ቃል አቀባዩ ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ብዙ መሪዎች በመድረኩ መሳተፋቸው፣ ከሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ክልሉ አንድ ጠንካራ አቋም መውሰዱና የኢጋድ የመተዳዳሪያ ደንብ መጽደቁ የጉባኤው ስኬታማነት መገለጫዎች መሆናቸውንም አምባሳደር መለስ ዓለም ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ የድርጅቱ መተዳዳሪያ ደንብ መፅደቅ ኢጋድን የበለጠ ያጠናክረዋል ብለዋል፡፡

ድርጅቱን ለሶስት አመታት የመሩት ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) ለቀጠናው ሀገራት ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም በጋራ መልማት ላሳዩት ቆራጥ አመራር በድጋሚ እንዲመሩ መመረጣቸው ሌላው የኢትዮጵያ ስኬት እንደሆነ ተጠቁሟል።

በመደበኛው የድርጅቱ ኢትዮጵያ ከሀገር አልፎ አፍሪካዊ አጀንዳ እንዲሆን እየተገበረችው የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የኢጋድ አባል ሀገራት ይህን ራዕይ ተጋርተውት የመርሃ ግብሩ አካል መሆናቸው ተጠቁሟል።

4ኛው የኢጋድ የመሪዎች መደበኛ ስብሰባ የአባል ሀገራት መሪዎች፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነርን ጨምሮ የአለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች በተገኙበት ባለፈው ማክሰኞ በጅቡቲ መካሄዱ ይታወሳል፡፡

በፍሬሕይወት ሰፊው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.