Fana: At a Speed of Life!

በዓለም ዙሪያ ከ50 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሀገር ውስጥ መፈናቀላቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) በዓለም ዙሪያ 50 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች በግጭት ወይም በአደጋ ምክንያት በሀገር ውስጥ መፈናቀላቸውን የሀገር ውስጥ መፈናቀል መቆጣጠሪያ ማዕከል /የአይ.ዲ.ኤም.ሲ/ በሪፖርቱ አስታውቋል።

ማዕከሉ በዓመታዊ ሪፖርቱ እንዳስጠነቀቀው፥ የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ቀድሞውኑ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑና በሀገር ውስጥ ለተፈናቀሉ ሚሊዮኖች ተጨማሪ አደጋዎችን ሊያስከትል የሚችል አዲስ ስጋት ነው ብሏል።

ከ45 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ሰዎች በግጭት ምክንያት ቤታቸውን ጥለው ለመሸሽ መገደዳቸውንም ነው የገለጸው።

ተጨማሪ አምስት ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ እንደ የመሬት መንቀጥቀጥ እና ጎርፍ ባሉ የተፈጥሮ አደጋዎች መፈናቀላቸውን ማዕከሉ አስታውቋል።

በዚህም ግጭትን ወይም አደጋን የሚሸሹ ነገር ግን በራሳቸው አገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷልም ነው ያለው።

ለቁጥሩ ማሻቀብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር በ2019 የተመዘገበው 33 ነጥብ 4 ሚሊዮን አዲስ የተፈናቃዮች ቁጥር ሲሆን፥ ይህ ቁጥር ከ2012 ጀምሮ በጣም ትልቁ በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ቁጥር ነውም ተብሏል።

እነዚህ ተፈናቃዮች ንጽህና በጎደላቸው ድንገተኛ መጠለያዎች፣ መደበኛ ባልሆኑ ሰፈሮች እና የከተማ መንደሮች የሚኖሩ በመሆናቸው አዲሱ የኮሮቫ ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል የሚያስፈልጉትን አካላዊ ርቀትን እና የንፅህና እርምጃዎችን ለመተግበር አስቸጋሪ እንደሚያደርገው በሪፖርቱ ተገልጿል።

መንግስታት ተፈናቃዮች በዚህ ከባድ የወረርሽኝ ወቅት የጤና እንክብካቤ እንዲያገኙ ማድረግ እንዲሁም ረዘም ላለ ጊዜ የመፈናቀላቸውን ምክንያቶች ለመቅረፍ እንዲሰሩ ተቋሙ ጥሪ አቅርቧል።

ከዚያም ባለፈ በሶርያ፣ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪብሊክ፣ በየመን እና በአፍጋኒስታን ያሉ ግጭቶችን ለመፍታት መስራት አለባቸው ብሏል።

አያይዞም የአየር ንብረት ለውጥን ለማስተካከል እና የተፈጥሮ አደጋዎች ለመከላከል መንግስታት እንዲዘጋጁ አሳስቧል።

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!

https://t.me/fanatelevision

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.