Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ መንግዶች ባለስልጣን በ11 ነጥብ 6 ቢለየን ብር ወጪ የ7 መንገዶች ግንባታ ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ መንግዶች ባለስልጣን በ11 ነጥብ 6 ቢለየን ብር ወጪ ሰባት መንገዶችን ለመገንባት የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈራረመ።

በዛሬው እለት የውል ስምምነት የተፈረመላቸው መንገዶቹ የሚገነቡት በአስፋልት ደረጃ ሲሆን፥ በአጠቃላይ 509 ነጥብ 11 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ አላቸው።

የመንገዶቹ የጎን ስፋት በገጠር 7 ሜትር በከተማ ደግሞ ከ 10 ሜትር ጀምሮ ስፋት እንዲኖራቸው ተደግርጎ የሚገነባ ይሆናል ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የስትራክቸር ስራ ፣ የአነስተኛ መፋሰሻ ቱቦ እና ድልድዮች ስራንም ያካተተ ነው።

ለግንባታቸው የሚውለው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን መሆኑም በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል።

የውል ስምምነት የተፈረመላቸው መንገዶቹም፦

1. ደብረ ብርሃን- ደነባ- ለሚ መገንጠያ እና ጅሁር- ደነባ

2. ፊቅ- ሰገግ- ገርቦ ደነን (ሎት 3. ዮአሌ – ደነን)

3. ሁምቦ- ጠበላ- አባያ-

4. ዳዬ- ግርጃ- ክብረ መንግስት (መልካ ደስታ) እና መለያ- መጆ መገንጠያ

5. ጅግጅጋ- ገለለሽ- ደገሃምቦ- ፈገግ (ኮንትራ 2)

6. ሀወላቱላ- ወተራራሳ- ያዩ- ውራቼ

7. ዛላምበሳ- አሊቴና- መረዋ- እዳጋሃሙር (ሎት 1. ዛላምበሳ- አሊቴና መገንጠያ) ናቸው።

መንገዶቹን ለመገንባት ጨረታውን አሸንፈው ከባለስልጣን መሥሪያቤቱ ጋር የውል ስምምነት ፊርማ ያደረጉት ስድሰቱ አገር በቀል ተቋራጮች ሲሆኑ አንዱ የውጭ ስራ ተቋራጭ ድርጅት ነው።

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነርር ሀብታሙ ተገኘ የመንገዶቹ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከዚህ በፊት በየአካባቢው የነበረውን የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍ የአካባቢው ህብረተሰብ በቀላሉ ወደ ፈለገው ቦታ የሚንቀሳቀስበትን ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረውም ለወጣቶች የስራ ዕድል እንዲፈጠር በማስቻል፣ በየአካባቢው የሚገኙ ትንንሽ መንደሮችና ከተሞችን እድገት ከማፋጠን እንዲሁም የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎች የማህበራዊ አገልግሎት ተቋማት እንዲስፋፉ ከማድረግ አንፃር የእነዚህ መንገዶች መገንባት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል።

የመንገዶቹ ግንባታ ለማጠናቀቀም ከሦስት እስከ አራት ዓመታት እንደሚወስድ ተጠቅሷል።

ጨረታውን አሸንፈው ከባለስልጣኑ ጋር የውል ስምምነት የፈጸሙት ተቋራጮች የመንገድ ግንባታው ስራውን በተያዘለት የጊዜ ገደብ እና ጥራት እንደሚያጠናቅቁ ገልጸዋል።

በለይኩን ዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.