Fana: At a Speed of Life!

በሜዲቴራኒያን ባህር ስደተኞችን የጫነች ጀልባ በመስጠሟ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተነገረ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በግሪክ የ79 ሰዎች ህይወት ከነጠቀው ስደተኞችን የጫነች ጀልባ አደጋ በኋላ ቁጥሩ ከዚህ የሚልቁ ስደተኞች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተነግሯል፡፡

ከጥቂት ቀናት በፊት በግሪክ ፍልሰተኞችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ በመስጠሟ 79 ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡

ጀልባዋ ፔሎፖኔዝ በተባለው የባህር ዳርቻ ከፔሎስ ከተማ በስተደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በሚገኘው ባህር ውስጥ መስጠሟን የግሪክ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች አስታውቀዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ እስካሁን ከጀልባዋ 104 ሰዎችን ማዳን ቢቻልም ፥ በጀልባዋ ውስጥ የነበሩ ተሳፋሪዎች ትክክለኛ ቁጥር እንደማይታወቅ ነው የተነገረው፡፡

ከምስራቃዊ ሊቢያ ወደ ግሪክ ባህር ስትቀዝፍ የነበረችው ጀልባ የመስጠም አደጋ ከደረሰበት በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ የበርካታ ሰዎች ህይወት ሳያልፍ እንዳልቀረ እየተነገረ ነው፡፡

ይህም በመካከለኛው ሜዲትራንያን ባህር ከደረሱ አደጋዎች የከፋ ያደርገዋል ብለዋል የሀገሪቱ ባለስልጣናት፡፡

ይህን ተከትሎም የቀድሞ የግሪክ የባህር ዳርቻ ጠባቂ አዛዥ ኒኮስ ለኢ አር ቲ ቴሌቪዥን እንዳሉት ፥ ከአደጋው በህይወት የተረፉትን የማግኘት እድል ዝቅተኛ ነው።

ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት በህይወት ከተረፉት ሰዎች ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ፥ ጀልባዋ ቢያንስ 40 ህጻናትን ጨምሮ ከ700 እስከ 750 ሰዎችን አሳፍራ ስትጓዝ እንደነበር ገልጿል።

በሌላ በኩል ዓለም አቀፉ የህጻናት አድርን ድርጅት ይህን ቁጥር ከፍ በማድረግ የህጻናቱ ቁጥር ወደ 100 ይጠጋል ብሏል፡፡

ባለፈው እሁድ የአሜሪካ ባንዲራ በተሰቀለበት ጀልባ ላይ የነበሩ 90 ፍልሰተኞች በግሪክ የባህር ጠረፍ አካባቢ የአደጋ ጥሪ ማድረጋቸውን ተከትሎ በአካባቢው በነበሩ የነፍስ አድን ሰራተኞች መትረፍ መቻላቸውን አልጀዚራ በዘገባው አስታውሷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.