ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በቤቱ አከማችቶ የተገኘው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በቤቱ አከማችቶ የተገኘ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ገለፀ።
ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር የዋለው ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ አከማችቶ ማስቀመጡን ኅብረተሰቡ ለፀጥታ አካላት በሰጠው ጥቆማ መሠረት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር በመኖሪያ ቤቱ በተደረገው ፍተሻ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በዚህም በተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት 64 የተለያዩ ዓይነት ሽጉጦች ፣ 587 የሽጉጥና የክላሽንኮቭ ጥይቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን መመሪያ በመጣስ 197 ሺህ 400 ብር አስቀምጦ በመገኘቱ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራው እየተደረገ መሆኑ መገለፁን ከፌደራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በተጨማሪም ከተጠርጣሪው ጋር በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ግንኙነት ፈጥሮ ሲሰራ እንደነበር ኅብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ መሠረት ፖሊስ በግለሰቡ ላይ ባደረገው ብርቱ ክትትል በቦሌ ክፍለ ከተማ ጎሮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተጠርጣሪውን ከአንድ ማካሮቭ ሽጉጥ እና ከተመሳሳይ 20 ጥይቶች ጋር በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራው እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ገልጿል።