Fana: At a Speed of Life!

ኮሚሽኑ ሕገ-ወጥ የሕጻናት ዝውውርን ለመግታት የቁጥጥር ሥርዓት ማጠናከር እንደሚገባ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሕገ-ወጥ የሕጻናት ዝውውርን ለመግታት የቁጥጥር ሥርዓት ማጠናከር እና በጋራ የግንዛቤ መፍጠር ሥራ መሥራት እንደሚገባ አሳሰበ።

ለሁለት ቀናት የሚቆይ በሕገ-ወጥ የሕጻናት ዝውውር ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ጉባዔ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው።

በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ወይዘሪት ራኬብ መሰለ ÷ ሕገ-ወጥ የሕጻናት ዝውውርን በመቀነስ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማስቀረት ኮሚሽኑ በልዩ ትኩረት እየሠራ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኮሚሽኑ ከሀገር ውስጥ ባለፈ የውጭ ፍልሰትን ለመቆጣጠርም ከዓለም አቀፍ ተቋማት እና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ጋር በትብብር እየሠራ እንደሚገኝ ገለጸዋል።

ሥደት የተሻለ አማራጭ አለመሆኑን ለማሳየት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ለሚመለከታቸው አካላት እየተሠጠ መሆኑንም ነው ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ የጠቆሙት።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ይገዙ በበኩላቸው ÷ በተለይ ለሕገ-ወጥ የሕፃናት ዝውውር መንስዔ ከሆኑ ችግሮች መካከል የዜጎች መሠረታዊ ፍላጐት አለመሟላት ዋነኛው መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህም መንግስት ዘላቂ መፍትሄ ለመሥጠት እየሠራ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

በየአካባቢው የሚገኙ የልማት ዐቅሞችን ወደ ተግባር በመለወጥ የዜጎችን ሕይወት ለመቀየርና የተጀመረውን የትምህርት ቤት ምገባ ሥራ ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሕገ-ወጥ ዝውውሩ የሚስተዋለው በራሳቸው ሚዛናዊ ውሳኔ መወሰን በማይችሉ ሕፃናት ላይ መሆኑ ጉዳቱን የከፋ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡

እልባት ለመሥጠትም ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ እንደሚጠናከር አስታውቀዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ በበኩላቸው ÷ በችግሩ ምክንያት ዘንድሮ በዞኑ በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት ሲገባቸው ያልተገኙ በብዛት ሕፃናት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ዋናው መንስዔም ጊዜያዊ ጥቅም ላይ ያተኮረ የአቻ ግፊትና የሕገ-ወጥ ደላሎች መበራከት መሆኑንም አንስተው ችግሩን ለመከላከል እና ሕገ-ወጦች ላይ አስፈላጊ እርምጃ ለመውሰድ እየተሠራ ነው ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ የዘርፉ ምሁራን የጥናት ውጤቶቻቸውን አቅርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ይጠበቃል።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት  ታከለ ታደሰ(ፕ/ር)÷ በዚሁ ኮንፈረንስ ባደረጉት ንግግር የሕፃናት ፍልሰት ያለውን አስከፊ ገፅታ በማወቅ ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር ምርምሮችን በማካሄድ የመፍትሔ ሐሳብ ለሚመለከታቸው አካላት መጠቆማቸውን ተናግረዋል።

 

ከዚህ ባሻገር ለፍልሰቱ እንደምክንያት የሚነሳውን ዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ወይም ድህነትን ለማስቀረት ለዚህ ችግር ተጋላጭ ለሆኑ  የሥራ እድል በመፍጠር የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.