በደቡብ ክልል በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን በላይ ችግኞች ይትከላሉ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በደቡብ ክልል ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን በላይ ችግኞች እንደሚተከሉ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በደቡብ ክልል የአረንጓዴ አዐራ ሁለተኛ ዙር ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ ሽገደ ቀበሌ ተካሄዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና በፓርቲው የደቡብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጥላሁን ከበደ እንዲሁም የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና የአካባቢው ማሕበረሰብ ተሳትፈዋል።
“ነገን ዛሬ እንትከል” በሚለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውብ የተፈጥሮ ገጽታ ባላት የጌዲኦ ዞን ችግኝ በመትከል ዐሻራችንን አኑረናል ሲሉ ከንቲባ አዳነች በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
የጌዲኦ ሕዝብ እና አባገዳዎች ላደረጉላቸው ደማቅ አቀባበልም አመስግነዋል፡፡
በክልሉ በሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የችግኝ ተከላ የፍራፍሬና ሀገር በቀል ዛፎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።
ከመርሐ ግብሩ ጎን ለጎንም በሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ በአንድ ዓመት ውስጥ ደርሶ ምርት መስጠት የጀመረ የእንሰትና ቡና ጥምር እርሻ ጉብኝት ተካሄዷል።