የተፈጥሮ ጋዝ ማቀነባበሪያ በኢትዮጵያ ለመገንባት የሚያስችል የጥናት ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተፈጥሮ ጋዝ ወደ ፈሳሽና ሌሎች ልዩ ልዩ የኢንዱስትሪና ፔትሮ ኬሚካል ግብአትነት የሚያገለግሉ የተለያዩ ይዘቶች ለመቀየር የሚያስችል ፋብሪካ እና ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ለማቋቋም የሚያስችል የ12 ወራት የጥናት ስምምነት ተፈረመ።
ስምምነቱ በማእድንና ነዳጅ ሚኒስቴር እና በግሪን ኮም ቴክኖሎጂስ መካከል ነው የተፈረመው።
የአሜሪካው ግሪንኮም ቴክኖሎጂስ ከሃዩንዳይ ኢንጅነሪንግ ኤንድ ኮንስትራክሽን ጋር በጋራ የሚያከናውኑት ይህ ፕሮጀክት ጥናቱ ተጠናቆ ወደ ትግበራ ሲገባ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል።
ለጥናቱ የሚያስፈልገው 70 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በኩባንያው ይሸፈናል ተብሏል።
የሚገነባው የማቀነባበሪያ ፋብሪካ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተፈጥሮ ጋዝን ወደ ተለያዩ ይዘቶች የሚቀይር ሲሆን፥ ናፍጣ፣ የአውሮፕላን ነዳጅ እንዲሁም ሌሎች የውበት መጠበቂያ ምርት አምራቾች ግብአትነት የሚያገለግሉ ምርቶችን የሚያቀርብ መሆኑ በጥናቱ ይረጋገጣል።
እነዚህ ግብአቶችም ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን የውጭ ምንዛሪ ለማዳን የተሰጠውን ሃገራዊ ተልዕኮ ለማሳከት እንደሚያስችል ነው ሚኒስቴሩ ያወጣው መግለጫ የሚጠቁመው።
ፕሮጀክቱ በነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ዘርፍ በሀገሪቱ ከተለዩት ስድስት የነዳጅ አለኝታ አካባቢዎች መካከል በሶማሌ ክልል ኦጋዴን ተፋሰስ ካሉብ እና ሂላላ ጨምሮ የተገኘውን 8 ትሪሊየን ኩዩብ ጫማ የሚገመት የተፈጥሮ ጋዝ እንዲሁም ቀጣይ ግኝቶችን ታሳቢ ያደረገ ነው።
በዛሬው ዕለት የተፈረመው ሌላኛው ስምምነት በትግራይ ክልላዊ መንግስት ልዩ ስሙ ምዕራብ ትግራይ ዞን ታህታይ አዲአቦ ክሩስ አሎስ ፒ ኤል ሲ ለተባለ ኩባንያ የኳርትዝ ማዕድን ፍለጋ ፈቃድ ለመስጠት የተከናወነ ነው።
ስምምነቱ ለሶስት ዓመታት የሚፀና ሆኖ ለ33 ኢትዮጵያውያን የስራ ዕድል የሚፈጥርና 6 ሚሊየን 187 ሺህ ብር ኢንቨስትመንት ካፒታል ያስመዘገበ ኩባንያ ነው።