አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 36 ክለቦች በ71 ምድብ እና በአምስት የውደድር ዘርፍ በሁለቱም ፆታ የሚሳተፉበት የአዲስ አበባ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ የክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ተጀመረ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ፌደሬሽን የበላይ ጠባቂ ማስተር ወጋየሁ በኃይሉ በመክፈቻ ሥነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶን ለማሳደግ የክለቦች ሻምፒዮና ውድድር አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ሳቦም አስማማው ጸጋዬ÷ የሻምፒዮና ውድድሩ የክለቦችን አቅም ከመፈተሹ ባሻገር ለኢትዮጵያ ሻምፒዮና ከተማውን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለማፍራት ያስችላል ብለዋል፡፡
ነገ በሚካሄዱ የፍፃሜ ውድድሮች አሸናፊ ለሆኑ ክለቦች እና ተወዳዳሪዎች የሜዳልያ፣ የዋንጫ እና የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት እንደሚበረከትላቸው የአዲስ አበባ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡