Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከቀድሞ የፖሊስ አመራሮች ጋር መከረ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በጡረታ በክብር ከተሰናበቱ የቀድሞ የፖሊስ አመራሮች ጋር በአዲስ አበባ ምክክር አካሄደ።

ፌደራል ፖሊስ ተቋሙን በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ሲመሩና ሲያገለገሉ ከነበሩ አመራሮች ጋር ተባብሮ መስራት ከዚህ ቀደም ያልተለመደ እንደነበር ተነስቷል፡፡

ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተቋሙን እድገትና ለውጥ ለማሳደግ ለውጥ ሲመኙ ከነበሩ ነባር አመራሮች ጋር ተቀራርቦ መስራትን የዕቅዱ አንዱ አካል አድርጎ እንደሚሰራ÷ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር እና የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ፕሬዚዳንት ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የጋራ መድረኮችን በማዘጋጀት ተቋማቸውን ባላቸው ፖሊሳዊ ዕውቀትና የካበተ ልምድ በሥራ ላይ ያለውን አመራር እንዲያግዙና እንዲያማክሩም አሳስበዋል፡፡

እነርሱን የሚጠቅሙ ዕድሎች ሲኖሩም የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተቋሙ ሁኔታዎችን ያመቻቻል ብለዋል።

የተያዘውን የለውጥ ጉዞ ውጤታማ ለማድረግ የቀድሞ የፖሊስ አመራሮችን የካበታ ልምድና ዕውቀት በመጨመር የምንመኘውን የፖሊስ ተቋም እንገነባለን ማለታቸውን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

የቀድሞ የፖሊስ አመራሮችም ከዚህ ቀደም ሲያገለግሉ ከነበረው ተቋማቸው ጋር በድጋሜ አብሮ ለመስራት መድረክ በመዘጋጀቱ አመስግነዋል፡፡

በቀጣይም ተቋሙ የጀመራቸውን የለውጥ ተግባራት በመደገፍ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.