ግብረ ሀይሉ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በኮቪድ-19 ምክንያት ከስራ የተፈናቀሉ ኢትዮጵያንን ለማገዝ እየሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) በተባበሩት አረብ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተቋቋው ግብረ ሀይል በኮቪድ-19 ምክንያት ከስራ የተፈናቀሉ ኢትዮጵያንን ለማገዝ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
ግብረ ሀይሉ በሰጠው መግለጫ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ሀይሉ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና አደረጃጀቶች ጋር ተቀናጅቶ የተመሰረተ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም ግብረሀይሉ ከተመሰረተ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ነው የተገለጸው።
በወረርሽኙ ምክንያት ከስራ ገበታቸው የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያንን ለማገዝ ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ በኢትዮጵያ የሚደረገውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ የተለያዩ ስራዎች በመስራት ላይ መሆኑን ተናግሯል።
በዚህም እስካሁን በኢትዮጵያ የሚደረገውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ በአቡዳቢ ከኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ማህበር ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚኖሩ በኮቪድ 19 ምክንያት ከስራ ገበታቸው የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን፥ በጥናት በተደገፈ አሰራር በተደረገው ድጋፍ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር እስከ ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ድረስ በአቡዳቢና አል አይን ለሚገኙ 674 ዜጎች ለአንድ ወር የሚበቃ የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ባሉበት ቦታ መድረሱን በመግለጫው ተመላክቷል።
ከዚያም ባለፈ በኢትዮጵያ የሚደረገውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከልና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያበረከቱትን የተለያዩ የንጽህና መስጫ ቁሳቁሶች፣ ማስክ፣ የእጅ ጓንት፣ ሳኒታይዘር እና የመሳሰሉትን ግብዓቶች በማሰባሰብ ላይ መሆኑ ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪ ግብረ ሀይሉ በተባበሩት አረብ ኢኤምሬቶች የሚገኙ ዜጎች በዚህ ወቅት የሚገጥማቸውን ችግሮች መፍትሄ በመስጠትና የጤና ችግር የገጠማቸውን የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ነውም ተብሏል።
ከዚያም ባለፈ ግብረሀይሉ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚገኙ ዜጎች ስለ ኮቪድ 19ኝ ወረርሽኝ በቂ ግንዛቤ ወቅታዊ መረጃዎች እንዲኖራቸው በመስራት ላይ መሆኑን አስታውቋል።