Fana: At a Speed of Life!

ሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች የ72 ሰዓት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደረሱ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች የ72 ሰዓት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል፡፡

ተፋላሚ ሃይሎቹ በአሜሪካ እና ሳዑዲ ዓረቢያ አደራዳሪነት ነው ለሶስት ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የደረሱት፡፡

የተኩስ አቁም ስምምነቱም ከዛሬ ጀምሮ የሚተገበር መሆኑን የአሜሪካ እና ሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አስታውቀዋል፡፡

የተኩስ አቁሙ በሁለቱ ሃይሎች መካከል በአየር ጥቃት ታግዞ የሚደረገው ጦርነት እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ የተደረሰ መሆኑን አር ቲ በዘገባው አስፍሯል፡፡

በትናንትናው ዕለት ብቻ በሱዳን መዲና ካርቱም በተፈፀመ የአየር ጥቃት አምስት ሕጻናትን ጨምሮ 17 ንጹሃን ዜጎች ለህልፈት መዳረጋቸው ተገልጿል፡፡

አሁን ላይ የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት የሰብዓዊ እርዳታ ለማሰራጨት እና ዜጎች ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀሱ ለማስቻል ያለመ መሆኑ በዘገባው ተመላክቷል፡፡

ሁለት ወራትን ባስቆጠረው የሱዳን ግጭት 2 ሺህ በላይ ዜጎች ለህልፈት ሲዳረጉ 25 ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ ለእርዳታ መጋለጣቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.